የአገር ውስጥ ቱሪዝም መጎልበት ለዜጎች እርስበርስ መቀራረብ ሚናው የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

61
ሐምሌ 12/2011 (ኢዜአ) የአገር ውስጥ ቱሪዝም መጎልበት ለዜጎች እርስ በርስ መቀራረብና ሰላም ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተጠቆመ። ኢትዮጵያ የበርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት ብትሆንም የቱሪዝም ዘርፉ በዋናነት የውጭ ጎብኝዎችን በመሳብ ላይ ያተኮረ ነው። ዘርፉን የሚመራው ተቋም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን የሚመራበት ራሱን የቻለ ስትራቴጂም አልነበረውም። ኢዜአ ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገራቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚሉት፤ የአገር ውስጥ ቱሪዝም መጎልበት ለአገር ሃብት ከመፍጠሩም በላይ ለዜጎች እርስበርስ መቀራራብና ሰላም ጉልህ ፋይዳ አለው። የአገር ውስጥ ቱሪዝም መስፋፋቱ በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች መካከል ያለውን ባህልና መስህብ በማወቅ በልዩነት ውስጥ ያለ ህብረ ብሄራዊነትን በመረዳት የአንድነትን መንገድ የሚዘረጋ ነው ብለዋል። የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በአመዛኙ ዜጎች ያሏቸውን እሴቶች በሚገባ ባለማወቃቸው የመጡ ናቸው ይላሉ። የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በማጎልበት በዜጎች መካካል መግባባትን በቀላሉ መፍጠር እንደሚቻል በመጠቆም። የአፋር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር በበኩላቸው የአገር ውስጥ ቱሪዝም መጎልበት በክልሎች መካከል  ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያሉት። በአፋር ክልል ያሉ የመስህብ ቦታዎችን መጎብኘት ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። ዜጎች የራሳቸውን እሴቶች በሚገባ ባወቁ መጠን አገራቸውን ይበልጥ ይወዳሉ ያሉት ደግሞ በድሬዳዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሽኩሪ አብዱራህማን ናቸው። ዜጎች በየአካባቢያቸው የሚመጡ ጎብኚዎችን በፍቅር በመቀበል ኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይ አገር መሆኗን በተግባር እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ማሚቴ ይልማ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ዘርፍ በተለምዶ ሲከወን መቆየቱን ያስታውሳሉ። ይህም ዘርፉን በተደራጀ መልኩ ለመምራት ከማስቸገሩም በላይ አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ሁለንተናዊ ፋይዳ አሳጥቷት ቆይቷል ነው ያሉት። ሚኒስቴሩ ይህን ለማስተካከል  ዘርፉ የሚመራበትን ግልጽ ስትራቴጂ በቅርቡ ተግባራ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም