በአማራ ክልልከአራት ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በምግብ ሰብል ለማልማት እየተሰራ ነው

111

ባህርዳር  ሐምሌ 12/2011 እየጣለ ያለው ዝናብ ለሰብል ልማት አመቺ በመሆኑ የእርሻ፣ የዘርና የአረም ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እንዳስቻላቸው በአማራ ክልል አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በአማራ ክልል ከአራት ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በምግብ ሰብል ለማልማት የእርሻ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ የማርወለድ ቀበሌ አርሶ አደር ዳኛቸው በቀለ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተያዘው ክረምት ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ በአካባቢያቸው መጣል በመጀመሩ የእርሻና የዘር ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ አስችሏቸዋል።

ካላቸው ሶስት ሄክታር መሬትም ሁለቱን ሄክታር በበርበሬ፣ ቀሪውን ደግሞ በበቆሎና ስንዴ ሰብሎች መሸፈናቸውን ገልጸዋል ።

በዞኑ ደንበጫ ወረዳ የእግዚአብሄር አብ ቀበሌ አርሶ አደር አብራራው ፈንቴ እንዳሉት ዘንድሮ ሶስት ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በመጠቀም በበቆሎ ሰብል እንዲሸፈን አድርገዋል ።

በምርት ዘመኑ አስፈላጊውን ግብአት በመጠቀም 150 ኩንታል ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን ያመለከቱት አርሶ አደሩ አሁን እየታየ ያለው የማዳበሪያ እጥረት በፍጥነት እንዲፈታ ጠይቀዋል ።

“የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡን ምክረ ሃሳብ ታግዘን የዘር ስራችንን በአግባቡ እያከናወንን ነው” ያሉት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤልያስ ወረዳ የጓይ ቀበሌ አርሶ አደር እንዳላማው ቢሻው ናቸው።

ካላቸው ሶስት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ሁለቱን ሄክታር በኩታ ገጠም እርሻ በስንዴ ሰብል ለማልማት የዘር ስራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸው ቀሪውን መሬት ደግሞ በበቆሎ፣ ጤፍና ሌሎች ሰብሎች ቀደም ብለው መሸፈናቸውን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩን በማገዝ ላይ ከሚገኙ ባለሙያዎቸ መካከል በወንበርማ ወረዳ የሰባዳር ካሎ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ አቶ ወርቅነህ ተስፋሁን እንደገለፁት በግንቦት ወር አጋጥሞ የነበረው የማዳበሪያ እጥረት ተፈትቷል ።

አርሶ አደሩ ከዘር ስራው በተጓዳኝ የአረምና ኩትኳቶ ስራውን በወቅቱ እንዲያከናውን እየታገዘ መሆኑንም ተናግራዋል ።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ በበኩላቸው በምርት ዘመኑ 4 ሚሊዮን 460 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት የእርሻና የዘር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

እስካሁንም የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ አንድ ሚሊዮን 800ሺህ ሄክታር መሬት ታርሶ በበቆሎ፣ በቢራና በምግብ ገብስ፣ በጤፍና ጥራጥሬ ሰብል ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

“በምርት ዘመኑ 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል “ብለዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ዩኒየኖች በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በወቅቱ ወደመሰረታዊ ማህበራ ማስገባት ባለመቻላቸው የተፈጠረ በመሆኑ ፈጥኖ እንዲፈታ ቢሮው እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት የመኽር ወቅት በክልሉ ከለማው አራት ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር መሬት 103 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።