''የሐረሪ ክልል አመራር አካላት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን አካተው መንቀሳቀስ አለባቸው''-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን

81
ሐረር ሐምሌ / 2011 ( ኢዜአ)  የሐረሪ ክልል አመራር አካላት የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን አካተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ። የክልሉ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት በአዲስ መልክ ተመስርቷል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በዚጉ ወቅት እንዳሳሰቡት አመራሩ የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠርና የ2012 ዕቅዱ አካል በማድረግ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ለዚህም የሰው ኃይልና በጀት በመመደብ የለውጥ ሥራ አድርጎ መሥራት ይገባዋል ብለዋል። ምክር ቤቱ በክልሉ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመግታት፣ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠርና ኅብረተሰቡን በማስተማር ስርጭቱን ለመቀነስ  እንደሚያስችል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። ክልሉ በአሁኑ ወቅት በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 2 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈሪያ መሐመድ ናቸው። በክልሉ በዚህ ዓመት 34ሺህ  የሚጠጉ ሰዎች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች አይ ቪ / ኤድስ የደም ምርመራ አድርገው 253 ቫይረሱ በደማቸው መገኘቱንም አስታውቀዋል። በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት እያንሰራራ  መምጣቱን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ቀደም ሲል በጥቅም ላይ የተመረኮዘ የመከላከልና መቆጣጠር እንቅስቃሴ መከናወኑ፣  ባለድርሻ አካላት  ያቀርቧቸው የነበሩት የግንዛቤ ሥራዎች መቆም ፣ ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰዎች፣  የጎዳና ተዳዳሪዎችና የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር መጨመር እንደሆነም አመልክተዋል። በውይይቱም የተገኙት አመራር አካላት በተለይ የአመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ፣የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች መቀዛቀዝና መሥሪያ ቤቶች የሥራቸው አካል አለማድረጋቸው ለቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት መንገድ ከፍቷል ብለዋል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መቆም፣ሥራውን ከለጋሽ ድርጅት በጀትና ድጋፍ ጋር ማያያዝ፣መዘናጋት ዋንኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በክልሉ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ አመራሩ በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉም  ተናግረዋል። የካቢኔ አባላት፣መሥሪያ ቤቶችን፣የአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች፣ አግባብ ካላቸው አካላትና መስሪያ ቤቶች የያዘ 36 አባላት ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ምክር ቤት ተመስርቷል። በሐረሪ ክልል በአገር አቀፍ ደረጃ በሚታየው የኤች አይ ቪኤድስ  ስርጭት በአራተኛነት ደረጃ ተቀምጧል። በሽታውን በመከላከል ረገድ የሚከናወኑ ሥራዎች መቀዛቀዛቸውና በተፈጠረው መዘናጋት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በውይይቱ ላይ ተገልጿል። ወጣቶች ለሱስ ያላቸው ተጋላጭነትም በሽታው መስፋፋት አንደኛው ምክንያት መሆኑን ተመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም