በካሜሮን ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ኢትዮጵያ ከኮትዲቯር፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር ተደልድላለች

70
ሐምሌ 12/2011 በ2021 በካሜሮን ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከኮትዲቯር፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር ተደልድላለች። የማጣሪያ ድልድሉ ይፋ የሆነው ትናንት ማምሻውን በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በተካሄደ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ነው። 48 ብሔራዊ ቡድኖችን በ12 ምድቦች ከፋፍሎ ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በምድብ 11 ከኮትዲቯር፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር ተደልድላለች። ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 ብሔራዊ ቡድኖች ቀጥታ ወደ ምድብ ድልድሉ የገቡ ሲሆን ሌሎች አራት ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ምድብ ድልድሉ በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚገቡ ይሆናል። ስምንት ብሔራዊ ቡድኖች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርጉት በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት እንደሆነ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ከመስከረም 27 እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ላይቤሪያ ከቻድ፣ ደቡብ ሱዳን ከሲሺየልስ፣ ሞሪሽየስ ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ እንዲሁም ጅቡቲ ከጋምቢያ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በደርሶ መልስ ያሸነፉት አራት ብሔራዊ ቡድኖች የምድብ ድልድሉን ይቀላቀላሉ። በዚሁ መሰረት የላይቤሪያና የቻድ አሸናፊ በምድብ አንድ ከማሊ፣ ጊኒና ናሚቢያ ጋር የሚመደብ ሲሆን የደቡብ ሱዳንና ሲሸልስ አሸናፊ ቡርኪናፋሶ ኡጋንዳና ማላዊ በሚገኙበት ምድብ የሚደለደል ይሆናል። የሞሪሽየስ ከሳኦቶሜና ፕሪንሲፔ አሸናፊ በምድብ ሶስት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ጋር የሚደለደል ሲሆን የጅቡቲ እና ጋምቢያ አሸናፊ ደግሞ በምድብ አራት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ አልጄሪያና ጋቦን ጋር ይደለደላል። ከምድብ ስድስት በስተቀር ከእያንዳንዱ ምድብ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ አገራት ቀጥታ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ይሳተፋሉ። በምድብ ስድስት ካሜሮን አዘጋጅ በመሆኗ በቀጥታ በውድድሩ የምትሳተፍ በመሆኑ በዚሁ ምድብ ከሚገኙት ኬፕቨርዴ፣ ሞዛምቢክና ሩዋንዳ አንዱ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ይሳተፋል። ካሜሮን የ32ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታስተናግድ ተመርጣ የነበረ ቢሆንም በዝግጅት ማነስ ምክንያት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ የካሜሮን አስተናጋጅነትን በመንጠቅ ለግብጽ መስጠቱ የሚታወስ ነው። ከሰኔ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በግብጽ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አልጄሪያና ሴኔጋል ከምሽቱ አራት ሰዓት በካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል። በግብጽ እየተካሄደ በሚገኘው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳታፊ አገራት ቁጥር ከ16 ወደ 24 ከፍ ማለቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም