ህዝቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የዞኑ የኃይማኖት ህብረት ጥሪ አቀረበ

65
ነቀምቴ ኢዜአ ሐምሌ 12/2011  …. በቄለም ወለጋ ዞን የሚታየውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታና አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥ ህብረተሰቡ አንድነቱን አጠናክሮ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የዞኑ የኃይማኖት ህብረት ጥሪ አቀረበ ። ህብረቱ ከአካባቢው የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ትናንት በደምቢዶሎ ስታዲየም የሰላም ኮንፈረንስ አካሔዷል ። በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ሃይሌ ኢየሱስ እንዳሉት ሠላም የሕዝቡ ሀብትና ንብረት በመሆኑ ሁሉም አንድነቱን አጠናክሮ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት። ሰላም የጋራ ሀብት በመሆኑ በኃይማኖት ፣በቋንቋና በዘር መከፋፈል ሳይኖር በጋራ ሰላምን ለመጠበቅ የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ህዝቡ ያለፈውን ሳይሆን የወደፊቱን በማሰብ በይቅር ባይነት መንፈስ የዞኑን ሠላምና ፀጥታ በመጠበቅ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል እጅ ለእጅ ተያይዞ ልማቱን ማፋጠን እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል። በደምቢዶሎ ከተማ የቢላል መስጊድ ይማም ሼህ ዛክር ሼህ ከድር በበኩላቸው በሰላም ወጥቶ መግባትና ሁሉም በየእምነት ቤቱ ተገኝቶ ማምለክ የማይቻልበት ደረጃ የተደረሰበትን መጥፎ ሁኔታ ለመለወጥ የሰላም ኮንፈረንሱ እንደተዘጋጀ ተናግረዋል ። ህዝቡ በኃይማኖትና በዘር ሳይከፋፈል የራሱን ሠላም ለማረጋገጥ አንድነቱን አጠናክሮና ከሥጋት ነፃ ሆኖ ፊቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ሼህ ዛክር ጥሪ አቅርበዋል ። በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የቤተል ወለጋ ሲኖዶስ ፕሬዚዳንት ቄስ ጫሊ ዮሴፍ እንደተናገሩት ደግሞ የኃይማኖት ተቋማት አንድነታቸውን አጠናክረው የዞኑን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከሕዝቡና ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። የዞኑ ህዝብ ከፀጥታ ችግር በመላቀቅ ወደ ልማት ሥራው እንዲገባ በፖለቲካ መስመር ልዩነት መቃቃር ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ለሰላም ጥሪው በጎ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል ። "የዞኑ ህዝብ በስታዲየም በመገኘት በአንድ ቃል ሠላም እንዲወርድ ፣ሕይወት ማጥፋትና ደም መፋሰስ እንዲቆም ያሰማው ድምፅ ለሰላም ያለው ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው "ያሉት ደግሞ በኮንፈረንሱ የተገኙት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስፍን አሰፋ ናቸው ፡፡ "በመሣሪያ ኃይል የሚመጣ ሠላም ዘላቂነት የለውም " ያሉት አቶ መስፍን መሣሪያ ያነሱ ኃይሎች መሣሪያቸውን አስቀምጠው ሕዝቡን ከማሸበርና ሠላም ከመንሳት በመላቀቅ ወደ ሰላማዊ ኑሮ መምጣት እንዳላባቸው አሳስበዋል ። መንግሥት የሕዝቡን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑንም  አረጋገጠዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ዴሬሣ  ከሁከትና በጥብጥ ትርፍ እንደማይገኝ በመግለፅ ሁሉም ለሰላምና ልማት እጅ ለእጅ ተያይዞ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም