ህዝቡን ወደልዩነትና ቅራኔ ለማስገባት በሚቀሰቅሱ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ ሊወስድ ይገባል-የደሴ ከተማ ነዋሪዎች

48
ኢዜአ ሀምሌ12/2011 በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህዝቡ እንዲለያይና ወደአመጽ እንዲያመራ ቅስቀሳ በሚያደርጉ አካላት ላይ የፌደራል መንግስት ፈጥኖ እርምጃ እንዲወስድ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት መቻቻልና አንድነትን ወደ ጎን በመተው ለፖለቲካ ጥቅም ህዝብን በሚያነሳሱ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ አለበት። በደሴ ከተማ የሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ የሱፍ ይመር እንዳሉት በየክልሉ የጎበዝ አለቃ እየተበራከተ መጥቷል፤ ለፖለቲካ ጥቅም ህብረተሰቡ ልዩነቱን እንዲያጎላና ቅራኔ ውስጥ ገብቶ ወደአመጽ እንዲያመራ የሚቀሰቅሱ አሉ፡፡ “በቅርቡ በአንዳንድ ክልሎች የተሰጠው የማይገባ መግለጫና የቃላት መወራወርም ያለልዩነት ተጋብቶና ተዋልዶ ለዘመናት የኖረውን ህዝብ ቅራኔ ውስጥ የሚያስገባ ነው” ብለዋል፡፡ አቶ የሱፍ እንዳሉት ኢትዮጵያ የተለያዩ አደጋዎች በተደቀኑባት ወቅት በክልል ያሉ አንዳንድ አመራሮች አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና መቻቻል ላይ አተኩረው መስበክ ሲገባቸው በየቀኑ አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ቃላት መለዋወጣቸው አግባብ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ድርጊቱ ኃላፊነት የጎደለው በመሆኑ የፌደራል መንግስት እነዚህን አካላት አቀራርቦ በማወያየት ተገቢ እርምጃ መውሰድና ችግሩን ፈጥኖ በመፍታት የህብረተሰቡን ደህንነት እንዲያረጋገጥ ጠይቀዋል። “በህዝብ ተጋድሎ የመጣውን ለውጥ ቀልብሶ ወደ ቀደሞ ጭቆና፣ ጥፋትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚስተዋልበት ሥርዓት ሀገሪቱን መመለስ የሚፈልግ ኃይል መኖሩን እያየን ነው “ ያሉት ደግሞ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ መኮንን አሰፋ ናቸው። የክልል ብዙሀን መገናኛዎች አገራዊ አንድነትን ዘንግተው በክልል ጉዳይ ላይ ብቻ በመታጠር የልዩነትና የሰላም ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል። የፌደራል መንግስት በእነዚህ ብዙሀን መገናኛና ህዝብን እርስ በእርስ ለማጫርስ በሚቀሰቅሱ አካላት ላይ ፈጥኖ እርምጃ በመውሰድ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ መኮንን ገለጻ የክልል አመራርም ሆነ ማንኛውም ፖለቲከኛ የግል ጥቅሙን ሳይሆን አገራዊ አንድነትንና ህዝብን በማስቀደም በኩል ራሱን መፈተሸ ይጠበቅበታል፡፡ ህብረተሰቡም የሴራ ፖለቲካን ተረድቶ በስሜት ከመነሳሳት ይልቅ ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ወንድሞቹ ጋር የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና አንድነቱን በማጠናከር የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡ “በፌደራል መንግስት እየተመሩ አብረን አንሰራም፤ አንታገስም በማለት ህዝቡን ከወንድሙ ጋር ለማጋጨት የሚሰሩ ኃይሎችን የፌደራል መንግስት በቸልታ መመልከት የለበትም” ያሉት ደግሞ በደሴ ከተማ የሚኖሩት ሸህ በድሩ መሀመድ ናቸው፡፡ መንግስት አለመግባባቶች ተባብሰው ሁከትና ብጥብጥ እስኪፈጠርና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እስኪደርስ ድረስ መጠበቅ የለበትም ሲሉም ተናግረዋል። “በወሬ የተገነቡ ሳይሆን የፈረሱ አገሮችን ነው የምናውቀው፤ እኛም ይህ እጣ ፈንታ እንዳይገጥመን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን” ብለዋል። እድገትና ውደቀት በሀገሪቱ ሊከሰት እንደሚችል በመገንዘብ ሁሉም ለአገር አንድነትና ለሰላም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በተለይ በቅርቡ አዴፓና ህወሓት ከገቡበት ያልተገባ የቃላት መግለጫና ውርወራ ወጥተው የህዝብን አንድነት በሚያጎለብቱና ለሰላም አስተዋጽኦ በሚኖራቸው ተግባራት ላይ አተኩረው እንዲሰሩም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም