በሲዳማ ዞንና ሀዋሳ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ

68
ሃዋሳ ኢዜአ ሐምሌ12/2011 በሲዳማ ዞን አንዳንድ አካባቢዎችና በሃዋሳ ከተማ ትናንት ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ። የዞኑ  ፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገነነው አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ አለታ ወንዶ ለኩ ፣ ሞሮቾና አለታ ጩኮ ተከስቶ የነበረው ችግር በመከላከያ ሠራዊት ፣ በፌዴራል ፖሊስና በክልሉ ልዩ ኃይል በቁጥጥር ስር ውሏል። በአካባቢዎቹ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር የደረሰው ጉዳት እየተጣራ መሆኑን አመልክተዋል። የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ተፈራ በበኩላቸው " በከተማው ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ውሏል"ብለዋል። በከተማው አላሙራ አቶቴና  መናኽሪያ  አካባቢዎች  መንገድ በመዝጋትና  ድንጋይ  በመወርወር  የፀጥታ  ችግር  ተፈጥሮ እንደነበርና  ነዋሪዎች ከፀጥታ ኃይሉጋር በመቀናጀት አካባቢውን ማረጋጋት መቻሉን  አስረድተዋል። የደረሰውን ጉዳትና ችግሩን ለማጣራት   እየተሰራ መሆኑን  አቶ መልካሙ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም