በምዕራብ ጎንደር ከ200 ሺህ በላይ የዕጣንና ሙጫ ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው

162
ጎንደር ኢዜአ ሐምሌ 12/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚደረግ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ከአካባቢው ስነ ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆኑ ከ200 ሺህ በላይ የዕጣንና ሙጫ ችግኝችን ለማልማት እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ በዞኑ ከ6ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረው የእጣንና ሙጫ ምርት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል። በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ባለሙያ አቶ ፋንታሁን ፍስሃ እንዳሉት  የሚተከሉ ችግኞች በረሃማነትን የሚከላከሉና ለአካባቢው ህብረተሰብ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን ጥቅም የሚሰጡ ናቸው ። ”ከ170 ሺህ በላይ ከፍተኛ የሙጫ ምርት የሚሰጡ ችግኞች ተፈልተው በየወረዳው በእጣንና ሙጫ ማምረት ስራ ለተሰማሩ ማህበራት በባለቤትነት እንዲከፋፈል እየተደረገ ነው ” ብለዋል፡፡ በአካባቢው ያለውን የእጣን ዛፍ ቁጥር ለማሳደግም በቂ ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆን ቆርጦ የመትከል ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል ። ተከላው በቂ የሆነ ዝናብና እርጥበት በሚያገኝበት በአሁኑ  ወቅት የሚከናወን በመሆኑ የዞኑ አመራሮች፣ የመከላከያ ሰራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት በተሳተፉበት ነው የተከላው ስራ እየተካሄደ ያለው፡፡ የእጣንና ሙጫ ችግኞቹ በዞኑ በሚገኙ መተማ ፣ ቋራና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ተዘጋጅተው እየተሰራጩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመተማ ወረዳ ለምለም ተራራ ቀበሌ ነዋሪውና በተፈጥሮ ሀብት ህብረት ስራ ማህበር በእጣንና ሙጫ ማምረት የተሰማራው ወጣት ሀሰን እንድሪስ እንደተናገረው አሁን ጥቅም እየሰጡት ያሉትን ዛፎች በመንከባከብ ተጨማሪ ችግኞችን የመትከል ስራ እያከናወነ  ነው፡፡ ”በዚህ ዓመት ብቻ በእጣንና ሙጫ ምርት በግል ከ40 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝቻለሁ ብዬ እጠብቃለሁ ” ያለው ወጣቱ ችግኞቹን በአግባቡ በማሳደግ ከዚህ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ በዚሁ ወረዳ ኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ባምላኩ ተመስገን በበኩሉ ከዚህ ቀደም በአካባቢው በተተከሉ ችግኞች ምክንያት በንብ ማነብ፣ በእንሳስት መኖና በሙጫ ምርት ተጠቃሚ መሆኑን ገልፆ "በዚህ አመት የሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም የበለጠ ተጠቃሚ ያደርገኛል" ብሏል ። በቋራ ወረዳ በእጣንና ሙጫ ማምረት ስራ የተደራጁ ማህበራት ሰብሳቢ ወጣት አስማማው በየነ " የእጣንና እና ሙጫ ዛፍ የኛንና የቤተሰባችንን ህይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ያሸጋገረ ስለሆነ ያሉትን ከመንከባከብና ከመጠበቅ ባለፈ ተጨማሪ ችግኞችን  ለመትከል ተዘጋጅተናል " ብሏል። በምዕራብ ጎንደር ባለፈው ዓመት ከተተከለው ውስጥም 78 በመቶ  መፅደቁንና የዞኑ የደን ሽፋን 31 በመቶ መድረሱን ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም