በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሳይበር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

57
ሐምሌ 11/2011 የሳይበር ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ስልጠና ዛሬ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መሰጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) በመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች በተሰጠው ስልጠና ላይ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የመስሪያ ቤቱ የካውንስል አባላት ተሳትፈዋል። ዓለም በምትገኝበት በ4ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ስለ ሳይበር ደህንነት ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ ስልጠናው ሲጀመር ገልጸዋል። "አሁን ባለንበት የኢንፎርሜሽን ዘመን የሳይበር ዲፕሎማሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና የዲፕሎማሲ መሳሪያ በመሆኑ በርካታ አገሮች ቅድሚያ ሰጥተው እየሰሩበት" ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ የተቀናጀ የሳይበር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲኖር የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይህንን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ማዘጋጀቱን በኤጄንሲው የሳይበር ድንገተኛ ምላሽ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ተመሰገን ገብረ ጻድቅ በበኩላቸው ተናግረዋል። በስልጠናውም የሳይበር ምንነት፣ የሳይበር ደህንነት፣ የሳይበር ዲፕሎማሲ፣ የሳይበር አንድምታ፣ የሳይበር ጥቃትና ተዛማጅ ርዕሶች ላይ ትኩረት ተደርጓል። በስልጠናው የተሳተፉ የመ/ቤቱ ካውንስል አባላት ሳይበር ቴክኖሎጂ በየጊዜው አዳጊና ተለዋዋጭ ከመሆኑ አንጻር መሰል ተከታታይ ስለጠናዎች ሊዘጋጁ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም