የምሁራን የጥናትና ምርምር ስራዎች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ችግር ለመፍታት የጎላ ሚና አላቸው

73
አዲስ አበባ ሀምሌ 11/2011 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የዘርፉ ምሁራን የሚያቀርቧቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች የጎላ ሚና እንዳላቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ። 17ኛው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ላጋጠመው የሚዛን መዛባት የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠቁመውን ጨምሮ 56 ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡ ተነግሯል። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት ባለሙያዎች አገሪቱ ለገጠማት የኢኮኖሚ ችግር በመፍትሄነት የሚያቀርቡት የጥናትና ምርምር ውጤት ወሳኝ ሚና አለው። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ለአገሪቱ የሚያቀርባቸው ምርምሮችና ጥናቶች ከፍተኛ እገዛ ነበራቸው። በኢኮኖሚው ዘርፍ ለምርምርና ጥናቶች የመነሻ ሃሳቦች፣ ለተማሪዎች የማጣቀሻ ጽሁፎችን በማቅረብ ተጠቃሽ ስራዎች ተሰርተዋል። እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ በተለይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለበትን ደረጃ እየገመገመ የሚያቀርባቸው ጽሁፎች ለፖሊሲ አውጪዎችና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች ነበሯቸው። በዘንድሮውም ጉባኤ መንግስት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራበት ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ የሚዛን መዛባት አስመልክቶ የሚቀርቡ ጥናቶችና የማሻሻያ ሃሳቦች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል። በቀጣይ የሚካሄዱ ምርምሮችን በማጠናከር የአገሪቱን ኢኮኖሚ የመደገፍ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደለ ፈረዳ በበኩላቸው በአገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረጉ በርካታ ጽሁፎች እንደሚቀርቡ ገልጸዋል። ማህበሩበየዓመቱየሚቀርቡጥናታዊጽሁፎችንበማቀናጀትለመንግስት ፖሊሲ አውጪዎች፣ለተቋማትናለተማሪዎችጥናታዊጽሁፍመነሻነትእንዲውሉይደረጋል። የሚቀርቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ካካተቷቸው ጉዳዮች መካከል አገሪቱ ለገጠማት የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት መፍትሔ የሚሆኑ ሃሳቦች ዋነኛ እንደሆነም ጠቁመዋል። ቀደም ሲል ከቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች መካከል የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ትራንስፎርም የሚያደርግበትን፣ የኢንዱስትሪውን እድገት አመላካች ሁኔታዎችና የወጪ ንግድን በማሻሻል ረገድ መሰራት ያሉባቸውን ተግባራት ያመላከቱት ይጠቀሳሉ። ማህበሩ ከ500 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን በጉባኤው በዘርፉ የተሰማሩ አለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው። ጉባኤው ለቀጣዮቹ ሶስት ቀናት ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም