ኢትዮጵያ የታክስ አሰባሰብና የወጪ ንግድ እድገቷን ማሻሻል እንዳለባት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አሳሰበ

92
በኢትዮጵያ ከማክሮ ኢኮኖሚው ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት የአገሪቱን የታክስ አሰባሰብ ስርዓት ማሻሻልና የወጪ ንግድን ማጠናከር የግድ መሆኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /አይኤምኤፍ/ አሳሰበ። ላለፉት በርካታ ዓመታት ፈጣን እድገት እያስመዘገበ እንደሆነ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ፈተናዎች እየገጠሙ መሆኑ ይነገራል። የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የወጪ ንግድ ዝቅተኝነት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በአይ.ኤም.ኤፍ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር አበበ አእምሮ እንደሚሉት ኢትዮጵያ እነዚህን ጨምሮ ከማክሮ ኢኮኖሚው ጋር በተያያዘ እየገጠሟት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ፈጣን እርምጃዎችን መውሰድ አለባት። በተለይም የታክስ አሰባሰብንና የወጪ ንግድን ከማጠናከር ባሻገር በአገሪቱ የምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የለውጥ እርምጃዎችን በስፋት መውሰድ እንደሚገባ በመጠቆም። እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጰያ ባለፉት 20 ዓመታት ከሌሎች ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ከተመዘገበባቸው የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ ነበረች። በተጠቀሱት ዓመታት ሰፊ የመሰረተ ልማት ስራዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነትና አዳዲስ የንግድ ስራዎች እንዲስፋፉ በማድረግ የተሻለ ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችላለች። ሆኖም ከእድገቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የታክሰ አሰባሰብና የወጪ ንግድ መሻሻል ባለመታየቱ በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ችግር መከሰቱን ነው በአይ.ኤም.ኤፍ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር አበበ የሚናገሩት። የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች ለመፍታት መንግስት የጀመራቸው የለውጥ እርምጃዎች ቀጣይነታቸውን ለማረጋገጥም በትኩረት መሰራት እንዳለበት የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም ባለስልጣን አመልክተዋል። በተለይም በከፍተኛ የውጭ ብድር እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቅ አገሪቱን ለብድር ጫና ዳርጓታል። ይህንን ለመፍታትም በጥናት የተደገፈ የኢኮኖሚ ሪፎርም ያስፈልጋልም ሲሉ ዶክተር አበበ ጠቅሰዋል። እንደ ዶክተር አበበ ገለፃ አገሪቱ የገጠሟትን የምጣኔ ኃብታዊ ፈተናዎች በፍጥነት መፍታት ከቻለች በዘርፉ ከፍተኛና ቀጣይነት ያለው እድገት የማስመዝገብ እድል አላት። የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ኢዮበ ተካልኝ በበኩላቸው አገሪቱ የገጠማትን የገቢና የወጭ ንግድ አለመጣጣም ችግር ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተወሰደ ነው ብለዋል። ከዚህም ሌላ በገቢ አሰባሰብ ረገድ ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል በተወሰደው እርምጃ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሩን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባከናወኗቸው የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ችግሩን መቀነስ ተችሏል፤ ይህም አገሪቱ የእፎይታ ጊዜን እንድታገኝ አስችሏታል ብለዋል። ከምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያሉትን መዋቅራዊ ችግሮች ለመፍታት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም