ችግኝ በመትከል ጤናማ አካባቢን እንፍጠር አሉ የህክምና ባለሙያዎች

81
ሐምሌ 11/2011 ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ ንፁህና ጤናማ አካባቢን እንፍጠር ይላሉ የህክምና ባለሙያዎች። የአቤት ሆስፒታል ሰራተኞች ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ከአንድ ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል። ለአረንጓዴ አሻራ ቀንም ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር 40 ሺህ ችግኝ ለመትከል ማቀዳቸውን አስታውቀዋል። በዚሁ ወቅት የሆስፒታሉ የአስተዳደርና ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይሌ መገርሳ እንዳሉት የሆስፒታሉ አመራርና ሰራተኞች ኀብረተሰቡን በህክምና ከማገልገል በተጨማሪ አካባቢን ጤናማ ለማድረግ የችግኝ ተከላውን አከናውነዋል። የችግኝ ተከላው በአገር አቀፍ ደረጃ ለቀረበው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ጥሪ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ሰራተኞቹ የአገሪቱን የደን ሽፋን ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ አሻራቸውን ያኖሩበትም ነው ብለዋል። ችግኞቹ በተራራማ ቦታ ላይ መተከላቸው ከስር ያለው ሐይቅ በደለል እንዳይሞላና በቂ ውሃ እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። ሰራተኞቹ በስፍራው በመገኘት ችግኞቹን እንዲንከባከቡ መታቀዱንም ገልፀዋል። የሆስፒታሉ ጠቅላላ ሀኪምና የበጎ ፈቃድ አስተባባሪ ዶክተር ቤዛዊት ንጉሴ ሆስፒታሉን አረንጓዴና ንፁህ ለማድረግ ከሚከወኑ ተግባራት ባሻገር አካባቢን ንፁህና ማራኪ ለማድረግ ችግኝ ተከላው መከናወኑን ተናግረዋል። ችግኝ ተከላ የዘመቻ ብቻ ሳይሆን እንደ ባህል እንዲዳብር የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል። ሰራተኞቹም ችግኞችን በዘመቻ ከመትከል ባሻገር እስኪፀድቁ ድረስ እንክብካቤ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ችግኝ መትከል ለአካባቢ ጥበቃና ስነ-ምህዳር እንዲሁም ለጤና አስተዋፅኦ ከማድረግ በተጨማሪ ስማችንን ተክለን አሻራችንን ለማቆየት የሚረዳ በመሆኑ የተከልናቸውን እንከባከባለን ያሉት ደግሞ ዶክተር ሄኖክ ደረጄ ናቸው። በተያዘው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ቀን ከ200 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ ይጠበቃል። የአቤት ሆስፒታልም ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ህክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ሀምሌ 22 ቀን 40 ሺህ ችግኞችን እንደሚተክል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም