በሐዋሳ የተጀመረው የጉምሩክ አገልግሎት አስመጪና ላኪዎችን በተቀላጠፈ መንገድ ለማገልገል ያስችላል- የጉምሩክ ኮሚሽን

162
ሐዋሳ ሐምሌ (ኢዜአ) 11 / 2011 በሐዋሳ በወጪና ገቢ ንግድ የተጀመረው የጉምሩክ አገልግሎት ለአስመጪና ላኪዎች በተቀላጠፈ መንገድ ለመስጠት እንደሚያስችል የጉምሩክ ኮሚሽንና ተጠቃሚዎች ገለጸ፡፡ የኮሚሽኑ የሃዋሳ ቅርንጫፍ በዚህ በጀት ዓመት 360 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጿል፡፡ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶ በከተማዋ የተጀመረው አገልግሎት መጨናነቅ በማስቀረት እንግልትን ይቀንሳል፡፡ አገልግሎቱ በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ይሰጥ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋት ሌሎች አስመጪና ላኪዎች እንደሚያሳትፍ አስረድተዋል፡፡ በዚህም አዲስ አበባና ሞጆ ድረስ ሄደው ሲገለገሉ የነበሩ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን በቅርበት ለማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ አገልግሎቱ የገንዘብና የጊዜ ብክነትን በመቀነስ ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ እንዲሁም አገልግሎቱ ቀልጣፋና በቴክኖሎጂ  ከማዘመን ባለፈ፤ በበቂ የሰው ኃይል ስለሚደራጅ በዘርፉ  የመልካም አስተደር ችግርን  እንደሚያቃልል አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከሚሰጠው አገልግሎት 360 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጸዋል፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጉምሩክ አገልግሎት ሲሰጥ በመቆየቱ ልምድ መኖሩን ያነሱት የጉምሩክ ኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘራኤል ላአ በበኩላቸው በአጭር ጊዜ ዝግጅት ሥራ መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ አገልግሎት የሚሰጡ መጋዘኖችና ትራንስፖርትን ያካተተ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ከሃዋሳ በተጨማሪ የሻሸመኔና የይርጋለም አምራቾች ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ የግዥ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ጣሰው ኢስጢፋኖስ ለፋብሪካቸው 80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን ጥሬ ዕቃዎች ለማስገባት ሞጆ ደረቅ ወደብ ሄደው ይረከቡ እንደነበር አስታውሰው፣በሃዋሳ በተጀመረው አገልግሎት ከሶስት ጊዜ በላይ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም የገንዘብ፣ የጊዜና የሰራተኞችን እንግልት በመቀነስ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስታውቀዋል፡፡ የክሩዝ ሎጂስቲክ ትራንዚተር አቶ ሽመክት መንግሥቱ  በበኩላቸው ወላይታ ሶዶ ለሚገኘው ፕሮጀክታቸው በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በኩል አገልግሎቱ ሲያገኙ እንደነበር ያወሳሉ። አሁን አገልግሎቱ ከፓርኩ ውጭ መስፋፋቱ ለአካባቢው አስመጪና ላኪዎች የጎላ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም