``የሐረሪ ክልል መንግሥት የቱሪስት መስህቦችን በመንከባከብና ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር አበረታች ተግባራት አከናውኗል-ሚኒስትር ሂሩት

59
ሐረር ሐምሌ 11 / 2011 የሐረሪ ክልል መንግሥት የተሪስት መስህቦችን በመንከባከብና ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ገለጹ። በፈረንሳይ መንግሥት በ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እድሳት የተደረገለት የባለ ቅኔና ደራሲ የአርተር ራምቦ የባህል ማዕከል ትናንት ተመርቋል። ሚኒስትሯ  ዶክተር ሂሩት ካሳው በማዕከሉ  ምረቃ ላይ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት በመስህቦች እንክብካቤና ለጎብኚዎች እየፈጠራቸው ያሉት ሁኔታዎች ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ናቸው። የክልሉ መንግሥት ከለጋሽ አገሮች ጋር በመቀናጀት ቅርሶች ይዘታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያከናውናቸው የጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች መጠናከርና ሌሎችም በአርአያነት ሊከተሏቸው ይገባል ብለዋል። የክልሉን ባህል መሠረት ያደረጉት የእንግዳ ማረፊያዎች ጎብኚዎች ተመልሰው እንዲመጡና ሌሎችንም ጭምር ይዘው ለመምጣት እንደሚያስችሉም ገልጸዋል። ሙዚየሞችንና ባህል ማዕከላትን በማስፋፋት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሥራ በመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት በሌሎችም አካባቢዎች መስፋፋት ያለበት ተሞክሮ መሆኑንም ሚኒስትሯ መስክረዋል። አምባሳደር ቦንተምስ በበኩላቸው ማዕከሉ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ከማጠናከርም በላይ፤ ቱሪዝምን ከማጎልበትና ለአካባቢው ማህበረሰብ በተለይም ለወጣቶችና ሴቶች ሥራ ከመፍጠር አንጻር ሚና እንዳለው ገልጸዋል። የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስትዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ለማዕከሉ የተደረገለት አድሳትና የተስፋፋለት አገልግሎት ቅርሱ ተጠብቆ እንዲቆይና ለጎብኚዎች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል እምነታቸውን ገልጸዋል። የፈረንሳይ መንግሥት በክልሉ በሚከናወኑ ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራዎች ላይ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። ማዕከሉ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ጥገና የተደረገለት ሲሆን፣ ውስጣዊ ቁሳቁስም ተሟልቶለታል። ጎብኚዎች የመኝታና የምግብ  አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጎ መገንባቱ ተገልጿል ። ራምቦ ወደ ሐረር ከተማ  የመጣው እንደ  አውሮፓውያን አቆጣጠር  በ1880 ሲሆን፣ ጀጎል በተባለው የከተማው መንደር ለ11 ዓመታት  መኖሩን ታሪክ ያወሳል። በስሙ የተሰየመው የባህል ማዕከል ባሉትታሪካዊ መጻህፍትና ቅርሶችን ጎብኚዎች እንዲመለከቷቸው በመደረግ ላይ መሆኑም በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል። የራንቦ የሐረር ቆይታ በፈረንሳይና በኢትዮጵያ መካከል ላለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጎልበት ሚና እንዳበረከተም ተወስቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም