ሙሽሮቹና ሚዜዎቻቸው በኢንዱስትሪ ፓርኩ 100 ችግኞች ተከሉ

98
ደሴ  ሐምሌ11/2011 በደሴ ከተማ በትናንትናው እለት የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን የፈፀሙ ሙሽሮችና ሚዜዎቻቸው በኮምቦልቻ በኢንዱስትሪ ፓርክ 100 ችግኞች ተከሉ ። አቶ አብደላ ሰይድና ወይዘሪት ሰሚራ አሊ የተባሉ ጥንዶች የሰርግ ስነ ስርዓታቸውን ያደመቁት በመዝናኛ ስፍራዎች ሳይሆን ሚዜዎቻቸውን በማስተባበር በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ችግኞችን በመትከል ነው ። ሙሽራው አቶ አብደላ ሰይድ በሰጠው አስተያየት ” በማግባቴ የተደሰትኩትን ያክል በሰርጌ እለት ችግኝ በመትከሌ ደግሞ ተጨማሪ ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ” ብሏል ። ሙሽሪት በበኩሏ ወደ መዝናኛ ቦታ እየሄዱ መስሏት እንደነበር ጠቅሳ በፓርኩ ቅጥር ጊቢ ደርሳ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም መሆኑን ስታውቅ ልዩ አድናቆትና ግርምት እንደፈጠረባት ተናግራለች ። በድርጊቱ መደሰቷንና ፕሮግራሙን ላዘጋጁት ሚዜዎቻቸውና ጓደኞቻቸው ምስጋና አቅርባ ችግኞቹ በተገቢው እንክብካቤ እንዲያድጉ አስፈላጊውን ሁሉ አደርጋለሁ ብላለች ። ሙሽሮቹ የተከሉዋቸው ችግኞች በፓርኩ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ”እንደመጀመሪያ ልጃችን በማየት በፍቅር እናሳድጋቸዋለን” በማለት ደስታቸውነ ገልፀዋል ። ሙሽሮቹ የተከሉት 100 ችግኞችን ሙሉ በሙሉ  እንዲፀድቁ ከፓርኩ ጋር ተገቢውን ክትትልና እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ፈፅመዋል ። የፕሮግራሙ አስተባባሪና  ሚዜያቸው ወጣት ጌትነት አያሌው በበኩሉ  የተተከሉት ቸግኞች እንዲጸድቁ  ክትትልና እንክብካቤ የሚያደርግ  ኮሚቴ ማቋቋማቸንን ገልጿል፡፡ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወጣቱን በበጎ ነገር እንዲሳተፍ በማድረግ አንድነትን፤ ሰላምንና መቻቻልን ለመስበክም እንደሚሰሩም ሙሽሮቹ ተናግረዋል፡፡ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንተግሬት ሰርቪስ ቡድን መሪ አቶ ጴጥሮስ በለጠ በበኩላቸው ኢንዱስትሪ ፓርኩ እስከ አሁን ድረስ ችግኝ ሳይተከልበት መቆየቱን ገልፀዋል ። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም እንደ አገር በሚካሔደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም መሰረት ኢንዱሰትሪ ፓርኩ 5 ሺህ ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዞ ነበር ። ሙሽሮቹ ድንገት መጥተው ትናንት ያካሔዱት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ያልተጠበቀና የመጀመሪያው ሆኖ መመዝገቡ ግን በእጅጉ አስደስቶናል ብለዋል ። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ችግኝ በመትከል አገራችንን ወደ አረንጓዴነት በመቀየሩ ሒደት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ሙሽሮቹ መልእክት አስተላልፈዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም