በወሊሶ ከተማ ለመንግስት ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ

60
አምቦ ሐምሌ 10/2011 በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ በማህበር ለተደራጁ ለ154 የመንግስት ሰራተኞች ትናንት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተሰጠ። የከተማው አስተዳደሩ ከንቲባ ወይዘሮ ካባ መብራቱ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በስምንት ማህበራት ለተደራጁት  የመንግስት ሰራተኞች 21ሺህ 560 ካሬሜትር ቦታ በእጣ ተከፏሏቸዋል። የተሰጠው ቦታ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ጥረት አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ሰራተኛች መካከል አቶ መታገል ተካልኝ በሰጠ አስተያየት በተሰጣቸው ቦታ መኖሪያ ቤታቸውን ሰርተው በግለሰብ የቤት ኪራይ የሚገጥማቸው ችግር እንደሚፈታላቸው ተናግረዋል። መምህር እንዳልክ መኮንን በበኩላቸው የቤት መስሪ ቦታ ማግኘታቸው ሥራቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ለማከናወን እንደሚረዳቸው ገልጸዋል፡፡ የእድሉ ተጠቃሚዎች ሰራተኞች መንግሥት በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የጀመረውን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደግፉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም