በአዲስ አበባ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት መጠን 3.4 በመቶ መድረሱን ጥናት አመላከተ

170
ኢዜአ ሀምሌ 10/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አዳዲስ አጋላጭ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ስርጭቱም 3.4 በመቶ መድረሱን ጥናት አመላክቷል። የከተማዋ ኤች.አይ.ቪ-ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ጥናቱ ባመላከታቸው የበሽታው ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ስርጭት፣ አጋላጭ ሁኔታዎች፣ ተጋላጭ ህብረተሰብ ክፍሎችን እና ስለወደፊት ስራዎቹ ከሴቶች ልማት ቡድኖች ጋር የንቅናቄ መድረክ ተካሄዷል። ውይይቱም በጥናቱ መነሻነት በጤና፣ በፀጥታ እንዲሁም በአጠቃላይ በማህበራዊ ሁኔታዎች ተሳትፎ ከሚያደርጉ 1 ሺህ በላይ የሁሉም ክፍለ ከተሞች የልማት ቡድን አባላት ተገኝተዋል። ተሳታፊዎች እነዳነሱትም የጤና ባለሙያዎች እስከ ቤተሰብ ወርደው ግንዛቤ ከማስጨበጥ ይልቅ በጤና ጣቢያዎች ላይ ብቻ ማተኮራቸው ችግሩን አባብሷል። ከአራዳ ክፍለ ከተማ የሴቶች ልማት ቡድን አባል የተገኙት ወይዘሮ አስካለ ታዬ፤  ከህብረተሰቡ  በበሽታው ላይ ያላቸው የግንዛቤ ደረጃ አመርቂ ባለመሆኑ ሁሉንም ነገሩን በምስጢርነት ይይዙታል ብለዋል። ወይዘሮ አስካለ አያይዘውም የጤና ባለሙያዎችም የግንዛቤ ፈጠራውን ወደ ሰፈር ዘልቀው የህብረተሰቡን ችግር በመረዳት ማስተካከያ ቢያደርጉ መልካም ነው ብለዋል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ የስነ-ህዝብና የጤና ሁኔታ ዳሰሳ ጥናት እንደ ሀገር ያወጣውን የጥናት ውጤት ተከትሎ የተደረገ ጥናት መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ የማህበረሰብ ንቅናቄ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ቦጋለ ገልጸዋል። እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ በከተማዋ የበሽታው ነባራዊ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱንና አዳዲስና ከተለመደው ውጭ የሆኑ ሁኔታዎችን እየስተዋሉ መሆኑን በጥናት መለየታቸውን ተናግረዋል። ሊቅ ወሲብን አስቀድሞ በልጅነት ዕድሜ የመጀመር ሁኔታዎች፣ ወሲብን ለገንዘብ ማግኛ መጠቀም፣ የአደንዛዥ ዕጾች በስፋት የመጠቀም፣ በድለላ ስራ የተሰማሩ አካላት መሳተፋቸውን ጥናቱ በአጋላጭነት ይዟል። የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ አማካሪ ወይዘሮ ዝማም ተበጀ በበኩላቸው በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት በተለይ በወሲብ ደላሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከፀጥታ ዘርፍ ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል። አደንዛዥ ዕጾችን ማዘዋወርን በድብቅ የሚሰሩ አካላትን ለመቆጣጠርም ጽሕፈት ቤቱ ከክፍለ ከተማና ከወረዳ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓቱ ጋር በጥናት ተለይቶ እንዲሰጥ ዝግጅት ላይ መሆኑን ወይዘሮ ዝማም ተናግረዋል። የጤና ባለሙያዎች እስከ ቤተሰብ ወርደው ግንዛቤ ማስጨበጫ ያለመስጠት ችግሩን እንዳባባሰውና ባሉት አጋላጭ መንገዶችም ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸው ተመላክቷል። ለዚህም አስገድዶ መደፈርና ያለ እድሜ መዳር ደግሞ ሁኔታዎቹን ያባብሳሉ። ችግሩ ስለሁኔታው መረጃ በሌላቸውና ከክልል በመጡት ላይ  በስፋት መስተዋሉን፣ የወሲብ ጓደኛ መቀያየርና ከጊዜ ወደ ጊዜ ኮንዶም የመጠቀም ፍላጎት መቀነስም ለስነ ተዋልዶ ችግሮች መንስኤ እንደሆኑም ተገልጿል። እንዲሁም ወንዶች ኮንዶምን የመጠቀም ግንዛቤ ቢኖራቸውም በአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ ወንዶች ስርጭቱን በማባባስ ሴቶች ተጠቂ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተነግሯል። ጥናቱ ላይ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ ኤች.አይ.ቪኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥናቱ ላይ ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም