ኮንፌዴሬሽኑ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅጃለሁ አለ

74
አዲስ አበባ  ሀምሌ 10/2011 የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በስሩ ያሉ ፌዴሬሽኖችን በማስተባበር ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን ገለጸ። በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ስራ ፈላጊዎችን መቀበል የሚችል አቅም አለ ብሏል። ወጣት ትዕግስት አሽኔ ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተመርቃለች። በምትኖርበት አካባቢ ያለው የወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ ለማድረግ እንቅስቃሴ ባለማድረጉ ወጣት ትዕግስት ስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን ትናገራለች። አዲስ አበባ ከተማ ከመጣችም ለሰባት ወራት ስራ ሳታገኝ እንደቆየች የምትናገረው ወጣት ትዕግስት ከወራት በኋላ በመዋዕለ ህፃናት መምህርነት እና በሽያጭ ባለሙያነት መስራቷን ገልጻለች። ሆኖም ግን የተሰማራችበት የስራ መስክ ከተማረችው የትምህርት ዘርፍ ጋር ተዛማጅ እንዳልሆነ ተናግራለች። በአሁኑ ወቅት ወጣቷ የኮምፒዩተርና ተዛማጅ ስልጠናዎችን ለሴቶች በሚሰጠው እንጦጦ ፕሮጀክት ክህሎቷን ለማጎልበትና ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ስልጠና እየወሰደች ትገኛለች። ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ስራ ለመቀጠር ከሚያስቡ ይልቅ ተደራጅቶ መስራትን ምርጫቸው ቢያደርጉ የተሻለ ገቢ ያገኛሉ የምትለው ወጣት ትዕግስት ለዚህ ደግሞ ወጣቱ ተደራጅቶ ስራ ፈጣሪ እንዲሆን መንግስትና ባለሃብቱ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብላለች። ''ከገንዘብ ችግር በስተቀር የስራ ፈጠራ ሀሳብ፣ አቅምና ጉልበት ወጣቶች ጋር ያለ በመሆኑ ባለሃብቱ ወጣቶችን በመደገፍ ለአገር ልማት አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት'' ስትል ተናግራለች። ስራ አጥ ወጣት በብዙ ጉዳዮች ላይ ተስፋ ስለሚቆርጥ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብላለች። ተመራቂ ተማሪዎችም በትምህርት ቤት ያገኙትን ትምህርትና የሰሯቸውን ፕሮጀክቶች አዳብረው ወደ ተግባር ለመቀየር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ወጣት አብዮት ከፍአለ እና ወጣት ብሩክ ሚሊዮን ሲሆኑ የሚመለከተው አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በስሩ ያሉ ፌዴሬሽኖችን በማስተባበር ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን ገልጿል። በተለይም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተመራቂ ተማሪዎችን በሙሉ የመቀበል አቅም እንዳለው የኮንፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ፍትህ ወልደሰንበት ለኢዜአ ገልፀዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከ20 የሚበልጡ ሆቴሎች በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ፍትህ በየክልሉም አዳዲስ ሆቴሎች እየተከፈቱ በመሆኑ በዘርፉ ችግር የለም ነው ያሉት። ኮንፌዴሬሽኑተደራጅተውመስራትለሚፈልጉወጣቶችም በስሩ ባሉ ኢንተርፕራይዞች በኩል ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። የግሉ ዘርፍ ልምድ የሌላቸውን ተመራቂ ወጣቶች እንዲቀጥር ኮንፌዴሬሽኑ እየመከረ ሲሆን በሌሎች ዘርፎች አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ስራ ስለሚገቡ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር የገለጹት አቶ ፍትህ ከሁሉም በላይ ለሰላም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አብራርተዋል። መንግስትበ2012 ዓ.ምለሦስት ሚሊዮን ዜጎችየስራዕድልለመፍጠርማቀዱ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም