የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በመጪው ሰኞ ይጀመራል

79
ባህርዳር  ሐምሌ 10/2011 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አራተኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ሐምሌ 15 /2011 በባህር ዳር እንደሚጀመር የክልሉ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው ፈንታ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉባኤው ለአራት  ቀናት  በሚያደርገው ቆይታ የክልሉን የ2011 በጀት ዓመት የአስፈፃሚ አካላት  የ11 ወራት ሪፖርት ላይ ይመክራል። የምክር ቤቱ ጉባኤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድርነት በዕጩነት የቀረቡትን የአቶ ተመስገን ጥሩነህን ሹመትንና የክልሉን የ2012 ረቂቅ በጀትን መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። በተጨማሪም  የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትና የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጠናቀቀው  በጀት ዓመት ሪፖርቶችን ያዳምጣል። ምክር ቤቱ  ሌሎች  ሹመቶችንም እንደሚያጸድቅ የሚጠበቅ መሆኑን  አቶ ምስጋናው ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም