የቡድን 20 አባል አገራት በአፍሪካ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ ድጋፍ ያደርጋሉ

47
ሐምሌ 10/2011 (ኢዜአ)በአፍሪካ የኢኮኖሚውን ስብጥርና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የቡድን 20 አባል አገራት ገለጸ። ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጀችውና የኢኮኖሚውን ስብጥርና የግሉን ዘርፍ ማሳደግ ላይ ያተኮረ "ቡድን 20 ከአፍሪካ ጋር ትስስር" ፕሮጀክት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። "የቡድን 20 ከአፍሪካ ጋር ትስስር" በጀርመን መንግስት አማካኝነት የተመረጡ የአፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጡ ለማገዝ በቡድን 20 አባል አገራት የተቋቋመ ፕሮጀክት ነው። በአውድ ጥናቱ የትስስሩ አካል የሆነችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያዊ ስብጥርና የግሉን ዘርፍ በሚያስፋፉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክከር ይደረጋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ። አገራቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ አድርገዋል፣ የግል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አሳድገዋል፣  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም እያስፋፉ ነው። ለዚህ ደግሞ የቡድን ሃያ አባል የሆነችው ጀርመን አፍሪካዊያን ለጀመሩት ኢኮኖሚያዊ እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል። ጀርመን ከአፍሪካዊያን ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ ለፕሮጀክቱ ስኬት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ታደርጋለችም ነው ያሉት። በአፍሪካ ኅብረት የጃፓን ተጠሪ አምባሳደር ፉሚዎ ሺሚዙ በአፍሪካ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ 'በቅርበት እንሰራለን' ብለዋል። በአህጉሪቱ  እንዴት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠርና በተለይም የግል ኢንቨስትመንት ዘርፉን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል 'ማሳወቅ እንፈልጋለን' ነው ያሉት። የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጡ እንዴት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ መዳበር እንዳለበት ልምዳንችንን እናካፍላለን ሲሉም አክለዋል። ለዚህ ደግሞ በአፍሪካ የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትና የመሰረተ ልማተ ማስፋፋት ላይ ለማገዝ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ በበኩላቸው የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ    መገኘቱን ተናግረዋል። በቀጣይም የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ፣ ምቹ የስራ ከባቢ ለመፍጠር እንዲሁም ተገማች ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት ትብብሩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም