የኤች. አይ.ቪ/ ኤድስ ስርጭት ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ተጠቆመ።

222
አዲስ አበባ ኤዚአ ሐምሌ 10/2011 በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት የተነፈገው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ በአዲስ አበባ ወጣቱን ትውልድ ለአደጋ እየዳረገ መሆኑን የከተማው ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የከተማው ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሥራ ተግባርን የተመለከተ ስብሰባ  ተካሂዷል። በዚህ ወቅት የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ሲስተር ብርዛፍ ገብሩ እንደገለፁት የኤድስ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት በተወሰደው ማህበረሰቡን ያሳተፈ ርብርብ በሽታው እያስከተለ የነበረው ጉዳት እንዳይስፋፋ መግታት ተችሎ ነበር። ሆኖም ባለፉት ዓመታት የበሽታውን ስርጭትና የሚያስከትለውን ሰብአዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳት ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እየተዳከመ በመምጣቱ፤ በህብረተሰቡ ዘንድም መዘናጋት በመፈጠሩ ችግሩ ዳግም እያገረሸ ትውልዱን ለአደጋ መዳረግ መጀመሩን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት በአሁኑ ወቅት 107ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ተረጋግጧል፤ ከዚህ ውስጥም ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው ብለዋል። በዚህም የሴቶች ቁጥር ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝና ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ትምህርትን ጨምሮ የግንዛቤ ማስፋፋት መርሃ ግብሮች መቀነስ ለበሽታው ዳግም ማገርሸትና መስፋፋት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል። በትምህርት ቤቶች ላይም ክበባትን የማደራጀት፣ የአቻ ለአቻ ስልጠና የመስጠት እንዲሁም ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ላይ ክፍተት እንዳለም ተነስቷል። እንዲያም ሆኖ በዚህ ዓመት የተለያዩ ክፍለ ከተሞችንና ወረዳዎችን በማቋቋም የድጋፍና ክትትል ስራ መሰራቱ የተገለጸ ሲሆን ከችግሩ ስፋት አንጻር ግን በቂ አይደለም ተብሏል። መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን የጠቀሱት ኃላፊዋ ከአሁን ጀምሮ የተለያዩ የንቅናቄ ተግባራት እንደሚከናወኑ አሳውቀዋል። ኤች. አይ.ቪ/ ኤድስ  ለሀገሪቱ ልማትና እድገት ፀር በመሆኑ ችግሩን ለመግታት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በባለቤትነት ሊሰራ  ይገባል ተብሏል። በኢትዮጵያ የኤች. አይ.ቪ/ ኤድስ ስርጭት ዳግም እያገረሸ ሲሆን በተለይም በአዲስ አበባ እና ጋምቤላ ክልሎች ችግሩ በከፋ ሁኔታ እየተስተዋለ መሆኑን ጥናቶች አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የኤች. አይ.ቪ/ ኤድስ ምክንያት በየዓመቱ የ16 ሺህ ሰው ህይወት እንደሚያልፍም በቅርቡ የወጣ መረጃ  ይጠቁማል። በአሁኑ ወቅትም ከኤድስ ቫይረስ ጋር የሚኖሩ ከ450 ሺህ በላይ ሰዎች የፀረ  ኤድስ መድሃኒት እንደሚወስዱም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም