ህዝበ ክርስቲያኑ ችግኝ ተከላውን ማጠናከር እንዳለበት ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ

100
አሶሳ /ደብረብርሃን ኢዜአ ሐምሌ 10 / 2011 ህዝበ ክርስቲያኑ ችግኝ የመትከልና የመጠበቅ ተግባሩን ማጠናከር እንዳለበት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን የአሶሳ ምዕራብ ወለጋ የጋምቤላ እና የደቡብ ሱዳን ሃገረ ስብከት ሊቀ-ጻጻስ ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ፡፡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንም  የችግኝ ተከላ ስራው እንደቀጠለ ነው። በአሶሳ ጌቴ ሴማኒ ቅዱስ ሩፋኤል ገዳም ምረቃ ወቅት  የተገኙ  እንግዶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡ የችግኝ ተከላውን የመሩት ብጹዕ አቡነ ሩፋኤል   ህዝበ ክርስቲኑ ችግኝ በመትከል እና በመንከባከብ አካባቢውን በዘላቂነት የመጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በችግኞች ተከላው የተሳተፉ  የኃይማኖቱ ተከታይ የሆኑ  የአሶሳ ነዋሪዎች የችግኞችን ልማት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ብሩህባንቺ ደስታየሁ በሰጡት አስተያየት የተራቆተውን አካባቢን እንዲያገግም የሚከናወኑ ችግኝ ተከላ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ “ከዚህ ቀደም ያለን ተሞክሮ ችግኝ ተክሎ መሄድ ብቻ ነው፤ ችግኞቹ ስለመጽደቃቸው ዋስትና እንዲሆን ተከታታይ ሥራ አልሠራንም ነበር” ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተገቢውን ውጤት እንዳልተገኘ ተናግረው የክረምቱ ዝናብ በመጠቀም የተከልኩትን ችግኝ በመንከባከብ እንዲጸድቅ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ወጣት ታሪኩ አዳሙ በበኩሉ የተከላቸውን ችግኞች እንዳይጎዱ አጥር በማዘጋጀት በዘላቂነት እንደሚንከባከብ ገልጿል፡፡ በችግኝ ተከላው ስነስርዓት  በእንግድነት የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንዲሁም የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሃብታሙ ታዬ እና ሌሎችም የህበረተብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአካባቢ ጥበቃን ለማጠናከር የሚያግዝ  የችግኝ ተከላ በ35ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል እንቅስቃሴ ተጀመረ። በአሳግርት ወረዳ በተጀመረው የተከላ ስነስርዓት ወቅት የዞኑ ግብርና መምሪያ  ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ኃይሌ እንደገለጹት መሬቱ  በደን ዛፍ ፣ በእንስሳት መኖና  ፍራፍሬ ተክሎች ይሸፈናል። ለዚህም ከ296 ሚሊዮን በላይ  ችግኞች ተዘጋጅተዋል። በልማቱ ከ473ሺህ በላይ ህዝብ ለማሳተፍ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ኃላፊው ስራው ሐምሌ 8/2011ዓ.ም  ሲጀመር በዕለቱ በኩታ ገጠም በተደራጁ  አርሶ አደሮችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ችግኞች በመትከል ድጋፋቸውን መግለጻቸውን አስረድተዋል። የተጀመረው የተከላ ስራ በዞኑን 22የገጠር ወረዳዎችና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ ነው ተብሏል። በአሳግርት ወረዳ የጎላ ቀበሌ አርሶ አደር ከበደ ሸዋንግዛው በሰጡት አስተያየት ከአምስት ዓመት በፊት በልቅ ግጦኝና በጎርፍ ለምነቱን ባጣ አንድ ሄክታር መሬታቸውን በባለሙያ ታግዘው ችግኝ እያለሙ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። አሁን ላይም  250ሺህ ብር ግምት ያለው የለማ ባህርዛፍ እንዳላቸውና ልማቱን አሁንም አጠናክረው መቀጠላቸውን አስረድተዋል። ሌላዉ አርሶ አደር ወንድሙ ሸዋንግዛው በበኩላቸው  ሁለት የውሃ  የውሃ ጉድጓዶችን በባህላዊ ዘዴ በመቆፈር ችግኝ አልምተው  ለአካባቢው አርሶ አደር በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል። በተከላው ስነስርዓት የክልሉን ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማርቆስ ወንዴን ጨምሮ ከ400በላይ የሚደርሱ የመንግስት ሰራተኞችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል። በዞኑ  በተፈጥሮና በሰው የለማ 255ሺህ 158 ሄክታር መሬት እንዳለ ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም