በአማራ ክልል በ31 ሺህ ሔክታር መሬት የቢራ ገብስ ልማት እየተካሔደ ነው

168
ሐምሌ /ኤዚአ 10/2011 በአማራ ክልል በተያዘው የመኽር አዝመራ በቢራ ገብስ ልማት ከ31 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር የመሸፈን ስራ እየተካሔደ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንየ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ለቢራ ገብስ ልማት ተስማሚ በሆኑ 9 ዞኖች የዘር የመሸፈን ስራው በተጠናክረ መንገድ እየተከናወነ ነው ። " በቢራ ገብስ ልማት ስራው 86 ሺህ አርሶአደሮች ተሳታፊ ሆነዋል "ያሉት ባለሙያዋ ደቡብ፣ ማዕከላዊና ሰሜን ጎንደር፣ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ሰሜንና ደቡብወሎ፣ እንዲሁም ሰሜንሸዋ ዞኖች ለቢራ ገብስ ልማት ተስማሚ ከሆኑ ዞኖች መካከል ይጠቀሳሉ ። እስከ አሁንም ከ17 ሺህ 400 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ታርሶና ለስልሶ በዘር ተሸፍኗል ። ባለሙያዋ "በቀጣይም በዕቅድ የተያዘውን መሬት ሙሉ በሙሉ በቢራ ገብስ ዘር ለመሸፈን በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና አጋር አካላት በቅንጅት አርሶ አደሩን እያገዙ ነው" ብለዋል። በቢራ ገብስ ለማልማት በዕቅድ ተይዞ የእርሻና የዘር ስራ እየተከናወነ ያለው መሬትም በቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ለምቶ ከነበረው በ12 ሺህ 778 ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል። ለቢራ ገብስ ልማቱ እስከ አሁን ድረስ 10 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያና 2 ሺህ 264 ኩንታል ምርጥ የቢራ ገብስ ዘር ለአርሶአደሮች ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል። በምርት ዘመኑ በዕቅድ የተያዘው መሬት በቢራ ገብስ ሲለማ ከ847 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል። ይህም አርሶአደሩ ከዘር እስከ ምርት ውቂያ ድረስ ያለውን የአሰራር ሂደት ጠብቆ ካለማ የጎንደር ብቅል ፋብሪካን የብቅል ገብስ ፍላጎት ማሟላት ይችላል ተብሏል። በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የዳት ቀበሌ አርሶ አደር ሞገስ ሲሳይ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በቢራ ገብስ ዘር እንዲሸፈን ማድረጋቸውን ተናግረዋል። የተሻለ ምርት ለማግኘትም አራት ኩንታል የምርት ማሳደጊያ ማዳበሪያ ገዝተውና የግብርና ባለሙያ በሚሰጣቸው ምክረ ሃሳብ ታግዘው ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ጠቁመዋል። ባለፈው ዓመት በቢራ ገብስ ካለሙት መሬትያገኙትን 30 ኩንታል ምርት ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ በማስረከብ 46 ሺህ 200 ብር ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። ዘንድሮም እያለሙት ካለው መሬት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ። በላይጋይንት ወረዳ የሞሰብ ተራራ ቀበሌ አርሶ አደር አለምነው ውቤ በበኩላቸው በቢራ ገብስ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ከ15 ዓመት በላይ እንደሆናቸው ገልጸዋል። አርሶ አደሩ እንዳሉት ባለፈው ዓመት አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በቢራ ገብስ አልምተው ያገኙትን 36 ኩንታል ምርት ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ በማስረከብ ከ55 ሺህ 400 ብር በላይገቢ  በማግኘት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ዘንድሮ ሩብ ሄክታር መሬት ብቻ በቢራ ገብስ ማልማታቸውን ገልጸው ቀሪውን መሬቱን ለማፈራረቅ በስንዴ የሰብል ዘር መሸፈናቸውን ጠቅሰዋል። ባለፈው የመኽር ወቅት በክልሉ በቢራ ገብስ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች ካለሙት 18 ሺህ 442 ሄክታር መሬት 358 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም