በሶማሌ ክልል ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ 212 አመራሮች ታገዱ

266

ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 በሶማሌ ክልል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ያልቻሉ በየደረጃው የሚገኙ 212 አመራሮች ከኃላፊነት መታገዳቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ አደን ፋራህ ገለጹ።
በጅግጅጋ ከተማ የክልሉ ሁሉም ወረዳዎች፣ዞኖች እና የከተማ አስተዳደር አመራሮች የተሳተፉበት የ2011 የበጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።

አቶ አደን እንደገለጹት የመድረኩ ዓላማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በወረዳዎቹ በጤና፣ በትምህርት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በውሃ ልማት እና በመልካም አስተዳደር የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና መፍትሄያቸውን በጋራ በመገምገም ለቀጣይ ስራ ግብዓት መውሰድ ነው።

“በተጨማሪም የዞን እና የወረዳ አመራር አካላት በግለሰብ ደረጃ ሂስ ግለሂስ በማድረግ የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡትን በማበረታታት በስራቸው ክፍተት ያሳዩ አካላት ላይ ደግሞ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ነው” ብለዋል።

በዚህ መሰረትም 212 አመራሮች ባሳዩት የስነ-ምግባር ጥሰት እና በአጠቃላይ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ያልተወጡ ስለመሆናቸው በግምገማው በመለየቱ መታገዳቸውን ተናግረዋል።

በግምገማው ተለይተው ከኃላፊነት እንዲታገዱ የተደረጉት አመራሮች አዲሱ የክልሉ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ የተመረጡ ነበሩ።

በየዞኑ በተናጠል የሚካሄደው ግምገማ በቀጣይ ቀናትም እንደሚቀጥል ታውቋል ።