አያ ጅቦና ድሬ

130

(እንዳሻው ሹሜ – ኢዜአ)

በጉዞ ከመድከማችን የተነሳ በኮስትሯ መኪና ውስጥ የተሳፈርነው የጋዜጠኞች ቡድን በድካምና መሰላቸው ባመጣው ዝምታ ውስጥ ተውጠን እያለ ነበር ከምሽቱ ሶስት ላይ ከተራራው ጫፍ ላይ ሆኘ በመስኮት ወደታች ስመለከት ሜዳ ላይ የፈሰሰ “ፍም እሳት” የመሰለውን የከተማዋን ብርሃን ያየሁት።

ብዙዎቹ በእንቅልፍ ሰመመን ውስጥ ግንባራቸውን ወንበራቸው ላይ አስደግፈው ስለተኙ፣ መኪናችን  የደንገጎን ተራራን ቁልቁለት እንደ ደራሽ ውሃ እየተግለበለበች መሆኗን እንኳን የምናውቀው በጣም ጥቂቶች ብቻ ነበርን።

ወደናፈቅናት ከተማ በምሽት መግባታችን ቅር ቢያሰኘንም ሁላችንም ባለዝናዋንና የምስራቋን ከተማ “ድሬዳዋን” ነግቶልን ለማየት እንደተመኘን አልቀረንም።

ይልቁንስ ሞቃታማውን አየር በሚያስታግሱት ጥቅጥቅ ባሉት የመንገድ ዳር ዛፎች ስር ባህሉ የሚፈቅደውን የሺቲ ቀሚስና ድሪያ ለብሰው ብርቱኳን፣ ቡና፣ ሳንቡሳና መሰል ምግቦችን የሚሸጡ ነዋሪዎችን እየተመለከትን ወደ ጥንታዊው የባቡር ጣቢያ ደረስን። ‘ድሬ’ ሞቅ ባለ አየሯ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገችልን።

የድሬዳዋን ከተማ ዘልቀን ስንገባ በአገራችን አንጋፋና ታዋቂ ድምጻውያን አንደበት የተንቆረቆሩ ዜማዎችን በእዝነ ልቦናዬ እያዜምኩ ነበር። ለድሬ ያላዜመ ማን አለ። ከዋናው መግቢያ በስተግራ በኩል ዝናዋ በዜማና በግጥም የተዘመረለት ”ሸክተፍ፣ ሸክተፍ – ይዞ ከተፍ” እያለ በረሃውን እያቋረጠ፣ያሰሳለፈውን የክፉና የደግ ትዝታ በሃዲዱ እያመነዠዘከ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠቱን አቋርጦ ለመቆዘሚያ ካፌ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ይመስላል። ህይወት ሩጫ፣ መክነፍ፣ መሄድና መንጎድ የነበረበት የድሬዳዋ ባቡር ጣቢያ ረግቶና ሰክኖ የካፌ አገልግሎት እየሰጠ አገኘሁት።

ገና ከመኪናችን እንደወረድን በአካባቢው የነበሩት ወጣቶች በቅንነት ወደኛ እየተቀላቀሉ ”አቦ ኮፍያ ስጡና!” እያሉ ሲጠይቁን ግማሹም እየሰጠ የቀረነው ደግሞ ዝም ብለን ወደ ምድር ባቡር ጣቢያ ግቢ ስንገባ ነበር አዛውንቱን አንዲትን መኪና ሲጠግኑ ያገኘኋቸው።

የባቡር ጣቢያው ግቢ ከላይ ቅጠሉ እንደ ዳስ በገጠመው ጥቅጠቅ ያለ ዘፍ ከስር ደግሞ ለአይን በሚታክት ግዙፍና በርካታ ብረታብረት፣ የባቡር ሃዲድና ተሽከርካሪ፣ አሮጌ መኪናዎች ብቻ ጥንታዊነቱን በዝምታ የሚናገሩ ቁሳቁሶች ሞልተውታል።

ሁሉም ጓደኞቼ ወደ ዋናው የባቡር ጥገና መጋዘን ውስጥ ሲገቡ እኔ መኪና ወደሚጠግኑት ሽማግሌ ጠጋ ብዬ ሰላምታ አቅርቤ እራሴን ሳስተዋውቃቸው በሚያጠግብ ፈገግታ ቀና ብለው ጨበጡኝና “አይነኩሉ ልመንህ እባላለሁ ምነው ወደኋላ ቀረህ” አሉኝ።

እንደ ዘንዶ በመሬት እየተምዘገዘገ አገር እሚያቋርጥ የነበረው ”ባቡሬ” በሚለው ዘፈን እንጂ በአካል የማላውቀው የበረሃው ጀግና ዛሬ ስራውን ቀይሮ ሻይ ሲሸጥበት ማየቴ እንደገረመኝ ነገርኳቸው። ይህንን በተናገርኩበት ቅጽበት ትዝታ የቀላቀለ ፈገግታ ፊታቸው ላይ አነበብኩ። በትዝታ ወደኋላ መለስኳቸው።

“ተያይዘን አረጀን ምን ዋጋ አለው፣ አሁንማ ምን ያልተቀየረ አለ ብለህ ነው ባቡሩም እኔም ውቢቷና ባለዝናዋ ድሬም ብትሆን እንደ ድሮዋ እኮ አይደለችም” ብለው ጨዋታቸውን ቀጠሉ።

መቼም ጥበብ የሚቀዳው ከገሃዱ ዓለም ነውና የድሬ ውበት ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው የባቡር እንቅስቃሴ የበርካታዜማዎች የግጥም ምንጭ ሆኖ ጆሮ ገብ የሆነ ሙዚቃ አጣጥመናል። አርቲስቶቹ ስለድሬና ባቡሩ ትስስስር፣ ስለከተማዋ ሰላማዊነት፣ ፍቅርና እንግዳ ተቀባይነት ብዙ ተብሎላቸዋል። በአይነ ስጋ አይቷቸው የማያውቅ ሰው እንኳን የሚያውቃቸው እስኪመስል ድረስ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ ታትመው ይናፈቁ ነበር።

እኔም ሃሳቤን ሰብስቤ ከአዛውንቱ አንደበት የሚንቆረቆረውን የትዝታ ወግ ለመስማት ጨዋታዬን ቀጠልኩ። አዛውንቱ አይነኩሉ ወደ ምድር ባቡር ከተቀላቀሉ አሁን 35 አመታት አስቆጥረዋል። በድርጅቱ ባገለገሉባቸው አመታት ከተራ መካኒክነት የመካኒኮችን ቡድን እስከ መምራት አገልግለዋል።

አቶ አይነኩሉ ድሬዳዋንና ባቡሩን ከልጅነት ጀምሮ አብረው አድገዋልና ትዝታቸውን ከቁጭታቸው ጋር ያጫውቱኝ ጀመር።

የድሬዳዋ መመስረት የፈረንሳይ መንግስት ኢትዮጵያን ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኘውን የባቡር ሃዲድ ከመዘርጋቱ ጋር ተያይዞ ስለነበር ከሁሉም የሃገራችን ክፍል የሚመጡ ሰዎች በፍቅር የሚያድሩባት፣ የሚበሉባት፣ የሚጠጡባት የሁሉ እናት የሆነች ቤት ነበረች።

በርግጥም ድሬ እህል ውሃ የጠራቸው እንደ ቤታቸው የሚኖሩባት፣ ያልቻሉት ደግሞ ትዝታቸውን ጥለው የሚያልፉባት የምትናፈቅ ከተማ እንደነበረች አዛውንቱ በትዝታ አይናቸውን አጨንቁረው ወደ ውስጣቸው እያሰቡ ነገሩኝ።

“ድሬ አሁንም ጥሩ ከተማ ነች ይሁን እንጂ ልክ ባቡሩ ባህሪውን ወደ ካፌ እንደቀየረው እኛም ያጣነው ብዙ ነገር አለ” የሚሉት አቶ አይነኩሉ ”በአሁኑ ወቅት ጥሩ ነገሮቿ እንዳሉ ሁሉ ድሮ ያልነበሩ ጎሳዊ አመለካከቶች፣ ከፍቅር ይልቅ የፖለቲካው ጫና የሚያዘምባት ከተማ ለመሆን እየተገደደች ነው” ይላሉ።

በተለይ  ሰውን እንደሰው ከማየትና ከማክበር፣ የጎረቤትን ልጅ እንደ ራስ ልጅ ወደ ክፉ ነገር እንዳይገባ ከመገሰፅ ሲብስም ከመቅጣት፣ የተጣላን ከማስታረቅ፣ የተቸገረን ከመርዳት፣ አብሮ ከመኖርና ከመተሳሰብ ጋር ያሉት ኢትዮጵያዊ ባህሎቻችን እንዳገርም እየጠፉ ስለሄዱ የድሬ የቀድሞ ስምና ባህሪም ልክ ወደ ካፌ እንደተቀየረው የጥንት ባቡር ድሬም የምትታወቅበትን የሰላምና የፍቅር ስም ሙሉ በሙሉ እንዳታጣ እፈራለሁ” ሲሉኝ እኔም የሚናገሩትን ከነባራዊ ሁኔታው ጋር በማገናዘብ ሃሳብ ውስጥ ተውጬ ነበር።

አቶ አይነኩሉ እንዳጫወቱኝ በርግጥም ያልተቀየረ ነገር ቢኖር ‘አያ ጅቦ‘ብቻ ነው” ።

‘አያ ጅቦ’ የምድር ባቡር ሰራተኞች የስራ መግቢያና መውጫ ሰአት መቆጣጠሪያ ደውል ሲሆን ይህን ስም ያገኘው በቀን ሶስት ጊዜ “አፉን ከፍቶ ስለሚጮህና ድምፁ የድሬዳዋን ከተማ ሙሉ በሙሉ የሚያዳርስ በመሆኑ ነው” ይላሉ አቶ አይነኩሉ።

“አያ ጅቦ” በርግጥም ልክ እንደ ጥንቱ ጠዋት፣ቀንና ማታ ሰአቱን ጠብቆ የሚጮህ ሲሆን አገልግሎቱ ግን ከስራ መውጫና መግቢያ ሰአት ከመቆጣጠር ባለፈ የድሬ ህዝብ አንድነትን የሚያሳይ ምስጢር በሆዱ ይዟል።

ምክንያቱ ደግሞ አያ ጅቦ ከተለመደው ሰአት ውጭ ከተሰማ በከተማዋ ውስጥ አንዳች ክፉ ነገር መከሰቱን የሚያበስር መሆኑ ሁሉንም የከተማዋንነዋሪዎች የሚያግባባና ችግሩን ለመመከት በአንድ ልብ፣ በአንድ ፍቅር የሚወጡበት ስለሆነ ነው።

አቶ አይነኩሉ እንደሚሉት፤ አያ ጅቦ በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ጊዜ የጦር አውሮፕላን ሲሰማ ወደ ምሽግ ለመግባት፣ እንዲሁም በከተማዋ የእሳት አደጋና መሰል ችግር ሲገጥም ህዝቡ ተባብሮ እንዲመክት በርካታ ጊዜ  ተጠቅሞበታል።

”አያ ጅቦ ዛሬም ሰአቱን ጠብቆ ቢጮኽም እንደ ድሮው የድሬ ህዝብ በአንድ ልብ፣በአንድ ፍቅር በነቂስ ወጥቶ ችግርን የሚከላከልበት መንፈስ አለ ለማለት እፈራለሁ” የሚሉት አቶ አይነኩሉ የማህበረሰቡ የመተሳሰብ፣ የአንድነትና የፍቅር ትስስር እንደ አገር በሚታየው የብሄርና የጎጠኝነት ፖለቲካ እየተሸረሸረ መምጣቱ አሳዛኝ ነው” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

በርግጥም በአሁኑ ወቅት ከአገር ሽማግሌዎች በላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሃሰትና የድፍረት ፖለቲካ የሚፅፍ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ይሰማል፣ እንደ ድሮው የጎረቤትን ልጅ መምከር፣ መቆጣት፣ ማስተማር ቀርቷል፣ ችግሮችን በሸንጎና በሽማግሌ፣ በመነጋገር የመፍታት ልምዳችን ይቅርና ሲመሽ ከእናት ከአባት ጋር ተሰብስቦ ማውራትም እየቀረ መሆኑ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን እየታየ መምጣቱን ታዝበዋል።

የድሬ ማንነት ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያዊ የሚያስብሉን አብሮ የመደሰት፣ አብሮ የማዘን፣ አብሮ የመብላት፣ የመተሳሰብና ሰላም ፈላጊነትን የሚያዳብሩ መልካም ባህሎቻችን አደጋ ላይ ስላሉ ሁላችንም ልናስብበት ይገባል የአዛውንቱ ምልዕክት ነው።

የአዛውንቱ አይነኩሉ ትዝብትና መልዕክት እጅግ ብዙ ነገር ይነግረናል። በፍቅር ሁሉም ደስተኛ ሆኖ ይኖር ነበር። ፍቅር ሲጠፋ ግን ስጋትና ፍርሃት ይነግሳል።