የግብጽ ብሔራዊ ቀን በአዲስ አበባ የግብጽ ኤምባሲ በድምቀት ተከበረ

71
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 9/2011 የግብጽና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ የግብጽ አምባሳደር ኦሳማ አብድልካልክ ገለፁ። የግብጽ ብሔራዊ ቀን የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት ዛሬ በድምቀት ተከብሯል። አዲስ አበባ በሚገኘው ኤምባሲዋ በተከበረው በዓል ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር ሚስተር ኦሳማ አብድልካልክ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያና ግብጽ ለረጅም ክፍለ ዘመናት የዘለቀና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ታሪካዊ መሰረት ያለው መሆኑን ገልፀዋል። የአገራቱ የመንግስታት ግንኙነቱም በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ለረጅም ዘመናት ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ተብሎ ከሚጠቀሱ አገራት ተርታ እንደሚሰለፍም አብራርተዋል። ሁለቱ አገራት በባህልና በሀይማኖትም ጠንካራ ትስስር ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ፤ አሁን ላይ ሁለቱ አገራት የሚገኙበት የለውጥ ሂደት መጪው ጊዜ መልካም እጣ ፈንታ ይዞላቸው እንደሚመጣ የሚያሳይ ነውም ብለዋል። ግብጽ እንደ ተቀረው አለም ሁሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የሚመራውን የለውጥ ሂደትና በተለያዩ መስኮች እየመጡ ላሉት ውጤቶች አድናቆት እንዳላት ገልፀው ፤ ሌሎች ውጥኖች ከግብ እንዲደርሱም ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ በሚመሩት የለውጥ ሂደት በኢኮኖሚውና በሌሎች ዘርፎች ለውጦች መምጣታቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ ፤ በሁለቱ ጠንካራና ቆራጥ መሪዎች ይህ ውጤት ሊመዘገብ መቻሉንም ተናግረዋል። አምባሳደሩ አክለውም ወደ ኢትዮጵያ አምባሳደር ተደርገው ሲሾሙ ሁለቱን አገራት ወደ ላቀ ደረጃ በሚያሸጋግሩ ስራዎች ላይ እንዲሰሩ መመደባቸውን ተናግረው ፤ ራሳቸውን በኢትዮጵያ ግብጽ አምባሳደር ብቻ ሳይሆን በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር አድርገው እንደሚያዩም ጭምር ተናግረዋል። ሁለቱ አገራት በትብብር የሚሰሩባቸውን ጉዳዮችንም ለአብነት ያነሱት አምባሳደሩ ፤ የጤና ተቋማት በማሻሻል፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቴክኒክ ስልጠና እንዲሁም ሌሎች ዘርፎችን አንስተዋል። የሁለቱን አገራት የጋራ ተጠቃሚነት በሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ  ለማሸጋገር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል አምባሳደር ኦሳማ። የግብጽ ብሔራዊ ቀን በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር ጁላይ 23 የሚከበር ሲሆን የግብጽ አብዮት ቀንም በመባል ይታወቃል። በዓሉ በ1952 የግብጽ አብዮት ፈንድቶ የዘውዳዊ ሥርዓት በመገርሰሱ የግብጽ ሪፐብሊክ የተመሰረተበት እና ይህ ሁኔታም የነፃነት እንቅስቃሴ በተለይም በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ እንዲፈጠር የቀሰቀሰ ሁነት መሆኑም የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም