ለአማራ ክልል ሰላምና የህግ የበላይነት መረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አዴፓ አስታወቀ

71
ባህርዳር ኢዜአ ሀምሌ 9/2011  የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአማራን ህዝብ አንድነት በመጠበቅና የህግ የበላይነትን አስተማማኝ ደረጃ በማድረስ የክልሉን ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታወቀ። ድርጅቱ በስራ አስፈፃሚና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ያካሔደውን ስብሰባ ተከትሎ የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኽኝ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ስራ አስፈፃሚውም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴው ለውጡን ባለፈው አንድ ዓመት የመራበትን ሒደት ገምግሟል። በተለይ ባለፉት ዓመታት ከዴሞክራሲ ስርዓት ጋር ተያይዞ ሃሳብን በነፃነት ከመግለጽ ፣ በዴሞክራሲ መንገድ ከመደራጀትና በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ መሰረታዊ ክፍተቶች እንደነበሩም ለይቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ለውጡን በመራበት ባለፈው አንድ አመት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በተሄደው ርቀት ከሞላ ጎደል የተሻለ መሆኑንና እንዳይደናቀፍም የተሰራበት እንደነበር ማዕከላዊ ኮሚቴው በጥልቀት ገምግሟል። የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ከለውጡ ጋር ለይቶ በማንሳትም በማዕከላዊ መንግስት ደረጃ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር የተደረገበት ሁኔታ እንደነበር ገልጸው በዚህም ሀገራዊ ቅርፅ የያዙ ጥያቄዎችን ድርጅቱ በማንሳት የትግል ሂደት ውስጥ መሆኑን ማዕከላዊ ኮሚቴው በጥንካሬ መገምገሙን አስረድተዋል። “ለውጡን እንዴት መራነው በሚለው አጀንዳ በተነሱ መሰረታዊ ሃሳቦች ላይም ሰፊ ውይይት ማዕከላዊ ኮሚቴው በማድረግ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሰራበትን ሁኔታ በጥንካሬና በጉድለት ለይቶ ገምግሟል” ብለዋል። “በለውጡ ሂደት ያጋጠመን ተግዳሮት የሰላም እጦት እንደነበርና ይህም በተለይ የህግ የበላይነት ካለመከበር ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር በመሆኑ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል”ብለዋል። በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመሰረታዊነት የህግ የበላይነት ክፍተቶች የታዩበት፣ በወንድማማቾች መካከል ያልተገቡ ግጭቶች የነበሩበት፣ በርካታ ወገኖች የተፈናቀሉበትና ንብረታቸውን ያጡበት ወቅት እንደነበርም ገምግሟል። ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልሉ የተፈፀመው አስነዋሪ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራም በህግ የበላይነት መታጣት ባጋጠመ ተግዳሮት የመጨረሻው ጫፍ የተፈፀመበት እንደሆነም ተናግረዋል። ይህም የአማራን ህዝብ ታሪክ የማይመጥንና የመጨረሻው ይሆናል ብሎ ማዕከላዊ ኮሚቴው የሚያስበውና የሚመኘው ፀያፍ ድርጊት እንደሆነም አቶ አብርሃም ገልጸዋል። ከዚህ በመነሳትም ማዕከላዊ ኮሚቴው በቀጣይ የተፈጠረውን ችግር በተሟላ የህዝብ ንቅናቄ ፈተና የሆነውን የህግ የበላይነትን ለማስከበርና እንዳይጣስም በቁርጠኝነት ለመስራት ወስኗል ። ለዚህም የአማራ ክልልን ህዝቦች አንድነት ከመቸውም ጊዜ በላይ በመጠበቅና በማጠናከር በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አዴፓ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አስታውቀዋል። በተለይም የክልሉን ህዝብ በመከፋፈል ሰላሙ እንዳይረጋገጥ ሌት ተቀን የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው በህዝቡ መካከል ሊፈጠር የሚችል የአንድነት መላላት በቀጣይ ሊያጋጥመን አይገባም ሲልም በመግለጫው አስረድተዋል። “ችግሩ በተፈጠረበት ሰዓትም ፈጥኖ የደረሰው ህዝቡ ነው” ያሉት አቶ አብርሃም “አጥፊዎችን በየገቡበት እየተከታተለ በቁጥጥር ስር በማዋል ለሚመለከታቸው የህግ አካላት ያስረከበው ህዝቡ ነው” ብለዋል። በዚህም አርሶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪና ሰላም ወዳድ ወጣቶች ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት ለሰሩት ስራና ለከፈሉት መስዋዕትነት አዴፓ ምስጋና አቅርቧል። “የክልሉን ልማት ለማፋጠንም በኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በቀጣይ በማስተካከል ህዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆንም ይሰራል” ብለዋል። የልማት ክፍተቶችን ለመሙላት አዴፓ ከሚያደርገው ርብርብ ጎን ለጎንም ሆን ተብለው የሚፈጠሩ የህግ ጥሰቶች ከመልካም ስነ-ምግባርና ከሞራል ጋር የሚቃረኑ አንዳንድ የንግድ አሻጥሮችና የቢዝነስ ስራዎችን እንደሚከታተልም አስታውቀዋል። የፀረ-ድህነት ትግሉን በማቀጣጠልም የክልሉን ልማት የላቀ ደረጃ ለማድረስና የአማራን ህዝብ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በጀመረበት አግባብ ዳር ለማድረስም አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም