ጨፌ ኦሮሚያ ለአዲሱ የስራ ዘመን ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

116
አዳማ  ሐምሌ 8/20011 (ኢዜአ) ጨፌ ኦሮሚያ ለአዲሱ የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ ከ70 ቢሊዮን  ብር በላይ በጀት አፀደቀ። የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶሎሳ ገደፋ ለጨፌው አስረኛ መደበኛ ጉባኤ በጀቱን አስመልክተው እንደገለጹት የክልሉ የበጀት ድልድል በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ይህም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ትልቅ  አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል። ለስራ ዘመኑ በጨፌው የጸደቀው በጀት ከፌዴራል መንግስት ድጎማ ፣ ከክልሉ ልዩ ልዩ  የገቢ ምንጮችና ከውጪ ብድር የሚሸፈን ነው። በጀቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 6 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል። የተያዘው በጀት ዓመት በዋናነት ለህዝቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ልማት መስኮች ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው “መንግስት በጀቱ ለተመደበለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ይሰራል” ብለዋል። በጨፌው የበጀትና የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይልማ ወየሳ የበጀት ድልድሉን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ለወረዳዎችና ለከተማ አስተዳደሮች በፍትሃዊነት  ሊያሰራ የሚያስችል የበጀት ድልድል መደረጉን አመልክቷል ። የጨፌው አባላት በበኩላቸው እያደገ የመጣው የክልሉ በጀት ያለምንም ብክነት በተፈለገው ዓላማ እንዲውል በየደረጃው የሚገኙ የስራ አስፈጻሚዎች ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል። በጀቱ ለተገቢው ዓላማ ማዋሉን ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግም የጨፌው አባላት  በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል። የጨፌኦሮሚያ አስረኛ መደበኛ ጉባኤ የዛሬ ውሎ መረሀ ግብሩን  ያጠናቀቀ ሲሆን ነገ የተለያዩ ሹመቶችና አዋጆችን በማጽደቅ እንደሚጠናቀቅ  ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም