እንግሊዝ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም የሚያስችል መርኃ ግብር ይፋ አደረገች

61
ሐምሌ 8/2011 (ኢዜአ) እንግሊዝ በአፍሪካ የአየር ንበረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም የሚያስችል መርኃ ግብር ይፋ ማድረጓን የዓለም አቀፍ ልማት ዋና ፀኃፊ ሮሪይ ስቴዋርት ገለፁ። ዋና ፀኃፊው ይህንን ይፋ ያደረጉት በኬንያ ባደረጉት የሁለት ቀናት ጉብኝት ወቅት ነው። ድጋፉ ከሰሀራ በታች የአፍሪካ አገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚገጥማቸውን ችግር ለማቋቋምና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት አቅማቸውን ማጠናከር ለሚያግዙ ተግባራት የሚውል ነው ተብሏል። በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለሚተገበረው ለዚሁ መርሃ ግብር 250 ሚሊዮን ዩሮ እንደተመደበም አመልክተዋል። የአፍሪካ አገራት ከማገዶ የሃይል ምንጭ ወደታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነት እንዲሸጋገሩ ማድረግ የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ተግባር መሆኑም በዚሁ ጊዜ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ድንገተኛ አደጋዎችን እያስተናገደች ነው የሚሉት ዋና ፀሀፊው የተበከለ አየር፣ የባህር ጠለል ከፍ ማለት፣ የሙቀት መጨመርን ለአብነት አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 600 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደሉም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደአየር ከሚለቀቀው አጠቃላይ የበካይ ጋዝ መጠን ውስጥ የአፍሪካ አገራት ድርሻ ከ2 እስከ 3 በመቶ የማይበልጥ ቢሆንም በዚህ ችግር ሳቢያ በዋነኝነት እየተጠቃች ያለችው ግን ይህው አህጉር ናት። ሁሉም አከባቢን፣ የዱርእንሰሳትንና ለአደጋ የጠጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመጠበቅ መሥራት እንደሚገባ ነው የዓለም አቀፍ ልማት ዋና ፀኃፊ ሮሪይ ስቴዋርት ያሳሰቡት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም