በኦሮሚያ በጉድለት የተገኘ ከአንድ ቢለዮን ብር በላይ ተመላሽ እንዳልሆነ ተገለጸ

47
አዳማ ሐምሌ 8 / 2011 በኦሮሚያ ክልል ከተቋማት በጉድለት ተገኝቶ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መመለስ ከነበረበት ገንዘብ ውስጥ ከአንድ ቢለዮን ብር በላይ ተመላሽ እንዳልሆነ ተገለጸ:: የክልሉ ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኤሌማ ቃፔ የመስሪያ ቤቱን የ2011 በጀት ዓመት ሪፖርት ዛሬ ለጨፌ ኦሮሚያ አቅርበዋል ። ዋና ስራ አስፈጻሚው ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ በ474 ተቋማት ላይ የኦዲት ምርመራ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል። ከተቋማቱ ውስጥ በ408 የፋይናንስና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም 62 በሚሆኑት ላይ ደግሞ የስራ አፈፃፀም ኦዲት ምርመራ መደረጉን በሪፖርታቸው አመልክተዋል። በኦዲት ምርመራ ግኝቱ መሰረት ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ ሃሳብ ከተሰጠበት አጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ አንድ ቢሊዮን 100ሚሊዮን ብር ያልተመለሰ በመሆኑ ምክር ቤቱ ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል። ተመላሽ ያልሆነው በበጀት ዓመቱ በተቋማቱ በሂሳብ ምርመራ ከተገኘው 2 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ብር ውስጥ ነው። የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የኦዲት ጉድለት የታየባቸው ተቋማት ላይ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ አመልክተዋል። የህዝብሃብትለተፈለገበትዓላማብቻእንዲውልጠንከራድጋፍናክትትልእንዲደረግአስገንዝበዋል። ጨፌው የቀረበለትን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት በጥልቀት ከተወያየበት በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። የጨፌ ኦሮሚያ አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ከሰዓት በፊት በነበረው ውሎ የጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤትና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ አፅድቋል ። ጉባኤው ነገም ቀጥሎ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ይጠበቃል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም