አትሌት ደራርቱ ቱሉ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ስፖርት ላበረከተችው አስተዋፆ እውቅና ሊሰጣት ነው

119
ሀምሌ 8/2011 (ኢዜአ) አትሌት ኮለኔል ደራርቱ ቱሉ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ስፖርት ላበረከተችው ጉልህ አስተዋፆ በሰሜን አሜሪካ የሜሪላንድ ግዛት እውቅና ሊሰጣት ነው። በሰሜን አሜሪካ የታላቁ አፍሪካ ሩጫ አዘጋጅ ኖቫ ኮኔክሽንስ ለኢዜአ በላከው መረጃ በዋሽንግተን ዲሲ በመጪው እሁድ በሚደረገው  የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ከ20 በላይ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በክብር እንግድነት እንደሚሳተፉ አስታውቋል። በውድድሩ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ አሰፋ መዝገቡ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ሙሉጌታ ወንድሙ፣ ሀይሉ መኮንን ይበልጣል አድማሱ እና ግርማ ቶላ በክብር እንግድነት እንደሚሳተፉ ተገልጿል። የፊታችን አርብ ሀምሌ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ በሚካሄደው መርሃ ግብር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለአለም አቀፉ አትሌቲክስ ስፖርት ላበረከተችው አስተዋጾኦ የሜሪላንድ ግዛት የእውቅና ሰርተፊኬት አንደሚሰጣት ተገልጿል። የሜሪላንድ ግዛት የምክር ቤት አባል ሎርጅ ቻኩርዲያን እንደገለፁት፤ አትሌት ደራርቱ በኦሎምፒክ ስፖርት 10 ሺህ ሜትር ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ለቤት በመሆን የመጀመሪያዋ ጥቁር አትሌት በመሆን ለአለም አትሌቲክስ ባበረከተችው አስተዋፆ እውቅና ልንስጣት ፈልገናል ብለዋል። በኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና እያገለገለች በመሆኑ እና ለስፖርቱ እያበረከተች ያለችውን አስተዋፆም ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ተናግረዋል። የውድድሩ አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አበዛ በበኩላቸው ታሪክ የሰሩ አትሌቶች በክብር እንግድነት  መገኘት የሩጫ ውድድሩን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። የሩጫ ውድድሩ የተዘጋጀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት በሰሜን አሜሪካ ሶስት ከተሞች የነበራቸውን ጉብኝት መነሻ ያደረገ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጋር በነበራቸው ውይይት ቀኑ የኢትዮጵያ ቀን ሆኖ እንዲከበር የከተማው ከንቲባ መወሰናቸውን ተከትሎ መሆኑም ተገልጿል። በመሆኑም እሁድ ሃምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም "ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ" በሚል የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል። ውድድሩ በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤትና የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ ኖቫ ኮኔክሽንስ በሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅትና በዋሽንግተን ዲሲ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል። በውድድሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ከተጋባዥ ታዋቂ የአፍሪካ አትሌቶች ጋር የሚሳተፉበት መሆኑም ታውቋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም