በሃይል ማመንጨት የተሰማሩ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሃይል ማመንጨት የተሰማሩ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው
52
አዲስ አበባ ሀምሌ 8 /2011በሃይል ማመንጨት ዘርፍ የተሰማሩ 17 የእንግሊዝ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው። በአዲስ አበባ የእንግሊዝ ኤምባሲ እንዳስታወቀው፤ የኩባንያዎቹ ጉብኝት በኢትዮጵያ በሃይል ዘርፍ ያሉ አማራጮችን በማጥናት ኢንቨስት ለማድረግ ያለመ ነው። ኩባንያዎቹ በቆይታቸው ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማትና በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የሃይል ፍላጎት በየአመቱ በ30 በመቶ እየጨመረ መምጣቱን መግለጫው አስታውሷል። ይህንን ፍላጎት ለማሳካት መንግስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ታዳሽ ሃይልን ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ማድረጉን እንዲሁ። በመሆኑም በቀጣቹ ቀናት ጉብኝት የሚያደርጉት የእንግሊዝ ኩባንያዎች በአገሪቱ የሚገኙ ምቹ ሁኔታዎችን በማየት በሃይል ማመንጨት ዘርፍ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ይረዳቸዋል ተብሏል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 4 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ሃይል እያመነጨት እንደምትገኝ መግለጫው አስታውሷል። በዚህም ኢትዮጵያ የቀጣናው የሃይል መሰረት ለመሆን እያከናወነች ያለውን ተግባር ያግዛታል ተብሏል። አስራ ሰባቱ የእንግሊዝ ኩባንያዎች ጉብኝት በአፍሪካ የሚገኙ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመፈተሽ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።