በባህርዳር ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል መቸገራቸውን ነጋዴዎች ገለፁ

79
ባህርዳር ኢዜአ ሐምሌ 8/2011 በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ችግር ስራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ እንቅፋት እንደሆነባቸው በከተማው ነጋዴዎች ገለፁ። የአስተዳደሩ ከንቲባ በበኩላቸው "አለአግባብ የንግዱን ማህበረሰብ በሚያጉላሉ ሰራተኞች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል" ብለዋል ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የባህር ዳር ነጋዴዎች እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ የሚሰጠው የአገልግሎት አሰጣጥ የተንዛዛ በመሆኑ በቀጠሮ ብዛት ለእንግልት እያጋለጣቸው ነው። የንግድ ፈቃድን ለማደስ እስከ ግማሽ ዓመት ድረስ እንደሚጉላሉ አመልክተዋል። አቶ ገበየሁ አሳምኔ  ነጋዴ  ከስድስት ወር በፊት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የንግድ ማእከልና አፓርታማ  ለመገንባት በ46 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ገንዘብ  በጨረታ ተወዳድረው በሊዝ ክራይ ያሸነፉበት  4 ሺህ 700 ካሬ ሜትር መሬት እስካሁን እንዳልተረከቡ ተናግረዋል ። በክልሉ የሊዝ አዋጅ መሰረት በጨረታ ያሸነፉበት መሬት በ15 ቀናት ውስጥ እንደሚሰጣቸው የሚደነግግ ቢሆንም በሰበብ አስባቡ ቀጠሮ በማብዛት እስካሁን እንዳልተረከቡ ገልፀዋል ። የአግልግሎት አሰጣጡ ያልተገባ ጥቅም ከመፈለግና ከአቅም ማነስ የተነሳ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው አቶ ገበየሁ ጠቁመዋል ። "በከተማ አስተዳደሩ የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር አግልግሎት ፈላጊውን ነጋዴ ከማጉላላት በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ መሰብሰብ የሚገባውን ግብር እንዳይሰበሰብ ክፍተት የሚፈጥር ነው" ብለዋል ። በፕላስቲክ ምርቶች ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ አዲስ ኪዳን የተባሉ ነጋዴ እንዳሉት  በከተማ አስተዳደሩ የሚታየው የመልካም አስተዳድር ችግር ብቃት ያለው ባለሙያ በተገቢው ቦታ ካለመመደብ የሚነሳ ነው ። ከአቅማቸው በላይ የተሰጣቸው የኃላፊነት ቦታ በብቃት መፈፀም ስለማይችሉ በቀጠሮ ብዛት ባለጉዳይ እንዲሰላች እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል ። ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ የሚችለውን የንግድ ፈቃድ ማውጣትና ማደስ ስራዎች እስከ አንድ ዓመት ድረስ የሚወስድበት ጊዜ እንዳለ  ጠቁመዋል። የባህር ዳር ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ስለሁኔታው ተጠይቀው "በተደጋጋሚ ጊዜ ተመሳሳይ ቅሬታ እንደቀረበላቸው ገልፀው ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው "ብለዋል ። በአንድ በኩል የአቅም ክፈተት ያለባቸውን በማብቃት በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅማ ጥቅምን ፍለጋ ተገልጋዩን በሚያጉላሉ ሰራተኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱም አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም