በግብጽ ታስረው የነበሩ 32 ኢትዮጵያውያን ተፈተው ወደ አገራቸው ገቡ

50
ካይሮ ሰኔ/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ግብጽ ውስጥ ለዓመታት በተለያየ ምክንያት በእስር ላይ የቆዩ ኢትዮጵያውያንን አስፈትተው ወደ አገራቸው  እንዲመለሱ  አደረጉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብጽ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው በተመለሱበት ወቅት በግብጽ እስር ቤቶች ከአራት ዓመት እስከ አስር ወር በእስር ላይ የቆዩ ሕጻናትና ሴቶችን ጨምሮ 32 እስረኞችን ይዘው መመለሳቸው በአገሪቷ ታሪክ የመጀመሪያ ክስተት ነው። በተለያዩ ምክንያት በግብጽ እስር ቤቶች ሲሰቃዩ የነበሩት እስረኞች ተፈተው ወደ አገራቸው ሲመለሱ፤ ደስታቸውን የገለጹት በእንባ ነው። ከተፈቱት መካከል አንዳንዶቹ እንደገለጹት፤ የእስር ጊዜውን በስቃይ አሳልፈዋል፤ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ስላስፈታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል። እስረኞቹ የተፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር ተወያይተው በደረሱበት ስምምነት መሰረት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በሱዳን፣ በኬኒያና በሳውዲ ዓረቢያ የነበሩ እስረኞች ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸው የታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም