ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የ100 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ

312

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 8/2011 ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ለቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስራዎች የሚውል የ100 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ ለወጣቶች በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።

ድጋፉ ለጥቃቅን፡ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን ለማስፋፋትና ለስራ ፈጠራ እንደሚውል በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የድጋፍ ስምምነቱን የፈረሙት የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ድርጅት ከሊፋ ፈንድ ፎር ኢንተርፕራይዝ ዴቨሎፕመንት ቦርድ ሰብሳቢ ሚስተር ሁሴን አል ኖይስ እና የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ተገኝተዋል።

በእለቱ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ለጋዜጠኞች  በሰጡት ማብራሪያ ፤ ስምምነቱ ስራአጥ ወጣቶች የራሳቸውን አዳዲስ ሀሳብ በማመንጨት ሥራ እንዲፈጥሩ ያስችላል ብለዋል።

ወጣቶች የቢዝነስ ሃሳብ አፍልቀው ነገር ግን መሬት ላይ ለማውረድ የገንዘብ እጥረት እንደሚገጥማቸው ያነሱት ሚኒስትሩ ድጋፉ በርካታ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ያግዛል ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ድርጅት ከሊፋ ፈንድ ፎር ኢንተርፕራይዝ ዴቨሎፕመንት ቦርድ ሰብሳቢ ሚስተር ሁሴን አል ኖይስ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የፈጠራ ስራዎችን እንዲያግዝ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ከስምምነቱ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ሚስተር ሁሴን አል ኖይስ  የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።