በአዴፓና ህወሐት መካከል የታየው አለመግባባት በሰከነ መንገድ ሊፈታ ይገባል…የጨፌ ኦሮሚያ አባላት

54
አዳማ ኢዜአ ሀምሌ 8/2011  መንግስት በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/አዴፓ እና በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ህወሐት መካከል ሰሞኑን የታየው አለመግባባት በሰከነ መንገድ ሊፈታ ይገባል ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ አባላት ገለጹ። የጨፌው አባላት ይህን ያነሱት በአዳማ ከተማ ትላንት በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት 5ኛ የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው። ችግሩ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው የዓላማ አንድነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችልም ጠቁመዋል። ከጨፌው አባላት መካከል አቶ ቀጄልቻ ቁንጣ እንደገለፁት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና መሪ ድርጅቱ እየታየ ያለው ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ የበኩሉን እገዛ ሊያደርግ ይገባል። "የአዴፓና የህወሐት የሰሞኑ አለመግባባት በድርጅቱም ሆነ በሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ የሚፈጥር ነው" ብለዋል። "በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የምናየው የመግለጫና የቃላት ውርወራ እንዲቆም ሁሉም ህዝቦች መተባበርና በጋራ መስራት አለባቸው" ያሉት ደግሞ አቶ ጀማል አህመድ ናቸው። የድርጅቶቹ አካሄድ ህዝቡ በራሱ ትግል ባመጣው ለውጥ ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ የፌዴራል መንግስት የዜጎችን ሰላም፣ደህንነት፣ፍትህ፣እኩልነትና አንድነት የማስጠበቅ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል። እየታየ ያለው ተግባር የተገኘውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ወደ ኋላ በመመለስ በህዝቦች አንድነትና አብሮነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አሻ ቱሳ ናቸው። በጉዳዩ ላይ የፌዴራል መንግስት በአፋጣኝ ጣልቃ በመግባት መፍትሄ መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የክልሉ መሪ ድርጅት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ለመፍትሔው የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም