በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አሸናፊ ሆነ

74
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 8/2011  የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ሆነ። የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንትና ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁገብ ስታዲየም ተካሄደዋል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከምባታ ዱራሜን 41 ለ 29 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆን ችሏል። ኮልፌ በውድድር ዓመቱ 33 ነጥብ በመሰብሰብ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአንድ ነጥብ በልጦ ነው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ የሆነው። በዘንድሮው የውድድር ዓመት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከገጠመው ሽንፈት በስተቀር ሌሎች ጨዋታዎችን በማሸነፍ ኮልፌ ውጤቱን በዋንጫ አጠናቋል። የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አሰልጣኝ ስንታየሁ ደምሴ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ የቂርቆስ ክፍለ ከተማው ሱራፌል በልሁ ኮከብ ተጨዋች ሆነው ተመርጠዋል። ደረጀ ግርማና ኤፍሬም ጎሹ የኮከብ ዳኛ ሽልማትን ያገኙ ሲሆን ጎንደር ከተማ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። በፕሪሚየር ሊጉ ደረጃ ከአንድ እስከ ሶስት ላጠናቀቁት ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና መቐለ ሰብዓ እንደርታ የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ የሊጉ አሸናፊ ከሜዳሊያው በተጨማሪ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ለክለቦችና ለተጫዋቾች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ሲካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ውድድሩ ሲጀመር መከላከያ አሸናፊ የነበረ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም