በባህርዳር ከተማ ተጠርጣሪ ወንጀለኛን ለመያዝ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የሰዎች ህይወት አለፈ

89
ሀምሌ 8/2011 በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ በነፍስ ግድያ ወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ ለመያዝ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ትላንት ማምሻውን ለኢዜአ እንደገለጹት ድርጊቱ የተፈፀመው ሐምሌ 7/2011 ዓ.ም ከጥዋቱ 12 ሰዓት በዘንዘልማ ቀበሌ ልዩ ስሙ “በድሮ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪውን ይዞ ለህግ ለማቅረብ በተደረገ ከበባ ነው። "ግለሰቡ ከስድስት ወራት በፊት በተፈፀመ የነፍስ ግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ እጁን በፈቃዱ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ተጠይቆ እሰጣለሁ ሲል ከቆየ በኋላ አሁን ላይ እጄን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም በማለቱ ነው"ብለዋል። በዚህም ተጠርጣሪውን ለህግ ለማቅረብ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶ እሱን ለመያዝ የተንቀሳቀሱ የፀጥታ አስከባሪዎች ከበባ ላይ ሳሉ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ህይወታቸው ሊያልፍ መቻሉን ተናግረዋል። "ከሞቱት መካከልም ሁለቱ የአካባቢው የፀጥታ አስከባሪዎች ሲሆኑ አንደኛው ደግሞ የተጠርጣሪው ቤተሰብ ነው" ብለዋል። በተኩስ ልውውጡም አንድ የፀጥታ አስከባሪ በደረሰበት የመቁሰል አደጋ ወደ ሆስፒታል ተልዕኮ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት እንደሚገኝም አስረድተዋል። ተጠርጣሪው ቀደም ሲል በአካባቢው በስውር ወጣ ገባ እያለ ይኖር እንደነበር ተደርሶበት ክትትል መደረጉን ኮማንደር ዋለልኝ ጠቅሰው የተጎጂ ቤተሰቦች ለፍርድ እንዲቀርብ ተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል። ተጠርጣሪው ግለሰብ በተኩስ ልውውጡ ለጊዜው ቢሰወርም ተከታትሎ በቁጥጥር ስር በማዋል ለፍርድ ለማቅረብ የፀጥታ ኃይሉ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ኮማንደር ዋለልኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም