በበጀት ዓመቱ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚያመጡ ስራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል…አቶ ሽመልስ አብዲሳ

64
አዳማ ኢዜአ ሀምሌ 7/2011 በአዲሱ የበጀት ዓመት በክልሉ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት በ11 ነጥብ2 በመቶ ለማስመዝገብ ርብርብ እንደሚደረግ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ። እየተካሔደ ባለው የጨፌው ጉባኤ ላይ አቶ ሽመልስ ባቀረቡት የ2011 ዓ.ም ሪፖርትና የ2012 ዓ.ም እቅድ እንዳመለከቱት በአዲሱ በጀት ዓመት በዋናነት በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኢንቨስትመንትና የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ይደረጋል። በማህበራዊ ዘርፍም በተለይም ትምህርት፣ ጤና መንገድና ሌሎች ተያያዠ መሰረተ ልማቶች የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ በሚቻልበት መልኩ በጥራት እንደሚከናወን ገልጸዋል። የ2011/12 የምርት ዘመን 199ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በዋና ዋና ሰብሎች ለማግኘት መታቀዱን የገለጹት አቶ ሽመልስ በዚህም ከ6ሚሊዮን ሄክታር በላይ በዘር ለመሸፈን በሚደረገው ርብርብ እስከ አሁን 2ነጥብ7 ሚሊዮን ሄክታሩ መሸፈኑን አመልክተዋል። ለዚህም ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር መቅረቡን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ በገጠርና በከተማ የመሬት ወረራን ለማስቀረት ከአራት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አባወራዎች የመሬት ባለቤትነት ካርታ እንደሚሰጥ ገልጸው 1ነጥብ1ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በገጠርና በከተማ ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጠርም ተናግረዋል። በኢንቨስትመንት መስክም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታት የማነቃቂያ አሰራሮች ከመዘርጋት ባለፈ በተያዘው የበጀት አመት 54 ሺህ ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ልማት መዘጋጀቱን ተናግረዋል። “የከልሉ መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ፈጣን ልማትና ዕድገት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ለማስመዝገብ ርብርብ ያደርጋል” ብለዋል። የጨፌው አባላት በፕሮጀክቶች መጓተት፣ የጥራት ጉድለትና በህዝብ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ላነሱት ጥያቄ በክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የስራ ሃላፊዎችና በምክትል ፕሬዝዳንቱ ምላሽ ተሰጥቶበታል። የጨፌው 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የቀረበውን የ2011 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2012 በጀት አመት የመነሻ ዕቅድ በጥልቀት ተወያይቶበት በሙሉ ድምፅ አፅድቋል። የጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ አመት 5ኛ የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በነገው ዕለትም የሚቀጥል መሆኑን የወጣው መረሃ ግብር ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም