ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ዘጠኝ ቢሊዮን የሚደርሰው የዓለም ህዝብ

57
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 7/2011  እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 የዓለም ሕዝብ ቁጥር ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን እንደሚደርስ ተገምቷል። የዓለም ህዝብ እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ዘጠኝ አገሮች መሆናቸው ነው የተተነበየው። ከነዚህ ዘጠኝ አገሮች መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስቱ የአፍሪካ አገሮች መሆናቸውን ሲኤንኤን በሃተታው አስቀምጧል። በ2018 በተደረገ ጥናት መሰረት ህንድ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ዲሞክራቲንክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ታንዛንያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያና አሜሪካ በ2050 ዘጠኝ ቢሊዮን ለሚደርሰው የዓለም ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚወስዱ ነው የተገለጸው። በሺዎች የሚቆጠጠሩ ዓመታትን ወስዶ እንደ አቆጣጠር በ1987 አምስት ቢሊዮን የደረሰው የዓለም ህዝብ ከ32 ዓመት በኋላ ስምንት ቢሊዮን ሊሞላ እየተንደረደረ መሆኑ ነው ዓለምአቀፍ መረጃዎች የሚያመለክቱት። በአሁኑ ወቅት ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የደረሰውን የዓለም ህዝብ ቁጥር በመደነቅ የሚገልጸው የሲኤንኤን ጹህፍ፤ "አሁን 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሰከንድ ላይ ምልክት አድርጋችሁ ብትጀምሩ እስከ 2263 ዓመት ድረስ አትጨርሱም" ሲል የህዝብ ቁጥሩን ከፍተኛነት በአግርሞት ይገልጻል። የዓለም ህዝብ እስከ እ.ኤ.አ 2050 አሁን ባለው ላይ ሁለት ቢሊዮን ህዝብ እንደሚጨምር የተነበየ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ግማሹ ያህሉ የሚሸፍኑት ዘጠኙ አገሮች መሆኑ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሁኔታው በመሬት ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ ከወዲሁ ማሰብ እንደሚገባም ነው የሲኤንኤን ዘገባ አጽንኦት የሰጠው። በሌላ በኩል ቁጥሩ እንደ አጠቃላይ ይጨምር እንጂ ቀደም ሲል የህዝብ ቁጥር እድገትን ለመቆጣጠር በተወሰዱ እርምጃዎች አሁን ላይ የህዝብ ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጣ አገሮች እንዳሉም መረጃዎች ይጠቁማሉ። የመንግስታቱ ድርጅት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው 27 አገሮች የህዝብ ቁጥራቸው በአንድ በመቶ ወይንም ከዚያ በላይ ቀንሷል። የዚህም ምክንያትም በተለይም እንደ ቻይናና ጃፓን ባሉ አገሮች የመውለድ ምጣኔ በዝቅተኛ ደረጃ እንዲቀጥል መደረጉን ይገልጿል። የዓለም የመውለድ መጠን በአንድ ሴት በ1990 ከነበረው 3 ነጥብ 2 በ2019 ወደ 2 ነጥብ 5ና ከዚያ በላይ ዝቅ እንደሚል ተተንብዯዋል። ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች የሚኖር የህዝብ ቁጥር መጨመር አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር እድገትን በመቀነስ በኩል ተጽእኖ ያደርጋል። ለአብነትም ከሳህራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በ2050 የህዝብ ቁጥራቸው አሁን ካለው በእጥፍ እንደሚጨምር ግምት ተቀምጧል። በዚሁ ጊዜ የአለም አማካኝ የመኖር መጠን ከ72 ነጥብ 6 ወደ 77 ነጥብ 1 ዓመት ከፍ ይላል የሚል መላምት የተሰጠ ሲሆን፤ የኢኮኖሚ እድገታቸው ዝቅተኛ በሆኑ አገሮች በ7 ነጥብ 4 ያንሳል። በነዚህ አገሮች የእናቶችና የህጻናት ሞት፣ የኤድስ በሽታ እንዲሁም ግጭት ከፍተኛ መሆን አማካኝ የመኖር እድሜ ዝቅ እንዲል ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ናቸው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይጠቅሳል። በአብዛኞቹ በእነዚህ አገሮች የህዝብ ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑ በመጥቀስ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር መጨመር ለሚያስከትላቸው የሃብት መመናመን፣ ተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ አካባቢ ብክለት፣ በሽታ መስፋፋትና ለሌሎች ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ። የህዝብ ቁጥር መጨመር የሚያስከትለው ችግር ቢኖርም የመውለድ ምጣኔ ዝቅተኛ ከሆነ የአምራቹ ሃይል ቁጥር እየቀነሰ በአለም ምጣኔ ሃብት ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚኖረው የዘርፉ ምሁራን ያነሳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም