በኦሮሚያ ክልል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ እየተሰራ ነው - ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ

83

አዳማ (ኢዜአ) ሐምሌ 7/2011 የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር በተጓዳኝ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ በመሥራት ላይ መሆኑን  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በጨፌ ኦሮሚያ 10ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት የክልሉ መንግሥት የክልሉን ፀጥታ በማረጋገጥ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚ ለመደገፍ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በዚህም የክልሉ መንግሥት በሕዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፣በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያና  በጉጂ ዞን በታጠቁ ኃይሎች ላይ  እርምጃ  እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ሳቢያ ከተፈናቀሉ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በተደረገው ጥረት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑት መመለሳቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚ  በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን የተናገሩት አቶ ሽመልስ፤ ግብርና ፣ አገልግሎት ፣ ኢንዱስትሪ ና ማኑፋክቸሪንግ የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግበዋል ብለዋል።

በ2010/11 የምርት ዘመን በዋና ዋና ሰብሎች 155ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡንና በሁለት ዙር በተካሄደ  የመስኖ ልማት  ከ220ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱንም ተናግረዋል።

በተያዘው የክረምት ወቅት በተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ መስክ ከ900ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንም አስታውቀዋል።

ለአካባቢ ብክለት ምክንያት በሆኑ 33 ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም