የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከባለሃብቱ ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ተባለ

141

ኢዜአ ሐምሌ 7/2011 የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የባለሃብቱን ተሳትፎ በማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ የኢኖቬሽንና ሳይንስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ ለፈጠራና የምርምር ሥራዎች የሚሰጠው ሽልማት የፈጠራ ባለሙያዎችን እያነቃቃ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በሚኒስቴሩ የኢኖቬሽን ድጋፍና እውቅና ጊዜያዊ ቡድን መሪ ሊንዳ ግርማ እንዳሉት፤ የፈጠራ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ግኝታቸውን ህብረተሰቡን ወደሚጠቅም ምርት እንዲያሸጋግሩ የባለሃብቱ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

በፈጠራ ባለሙያዎች አዳዲስ ነገር የመስራት ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን የገለፁት ወይዘሪት ሊንዳ፤  ሆኖም አዲስ ነገርን ያለመቀበልና የመግፋት ሁኔታ ይታያል ብለዋል፡፡

“በብዙ ባለሃብቶች ዘንድ ወደ አዲስ ነገር ደፍሮ የመግባት ችግር ይስተዋላል” ያሉት ቡድን መሪዋ፤ ሃብታቸውን የሚያፈሱትም በአጭር ግዜ ገንዘብ በሚያስገኝላቸው ንግድ ላይ መሆኑን ና የፈጠራ ባለሙያዎች ብቻቸውን ለውጥ ማምጣት ስለማይችሉም የባለሃብቱ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግል የሚንቀሳቀሱ አምስት የፈጠራ ማእከላት እንዳሉ የተናገሩት ወይዘሮ ሊንዳ፤ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ካሉ የፈጠራ ማእከላት ጋር በቅንጅት ባለመስራታቸው ተመሳሳይ ፈጠራ እየሰሩ ነው አንዱ ለአንዱ አቅም የመሆን ውሱንነትም ይታያል ብለዋል፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ ለተለያዩ የፈጠራና የምርምር አሸናፊዎች ሽልማትና እውቅና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በውድድሩ ህጻናት፣ አዋቂዎችና ተቋማት እንደሚሳተፉ ገልፀው፤ ይህም ሳይንስን ባህሉ ያደረገ ትውልድ ከመፍጠርና የፈጠራ ባለሙያዎችን ከማነቃቃት አኳያ በጎ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የጠቀሱት።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ለ65 የምርምር ስራዎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት ቡድን መሪዋ፤ ገንዘብ በመመደብ እየተሰራ መሆኑና በተጠናቀቀው በጀት አመትም ለሶስት ምርምሮች ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ምርምሮቹ እስከ 3 አመት የሚፈጁ መሆናቸውንና 7ቱ ተመርቀው ለምርምሮቹ ቢዝነስ ፕላን ተሰርቶ ተደራሽ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊመቻች መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ከምርምሮቹ መካከል በቆዳና ሌጦ፣ በግብርና፣ በኤሌክትሮ ሜካኒክስ፣ በህክምና ና በኬሚካል ላይ ያተኮሩ የሚገኙበት ሲሆን፤ ይሄም  የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገቡና በትኩረት አቅጣጫ   የተለዩ ናቸው ተብሏል።

የቆዳና ሌጦ ጥራት መቀነስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በምርምር ተለይቷል ያሉት ቡድን መሪዋ፤  ግኝቱም የቆዳ ምርት ጥራት ለማሻሻል ለሚመለከታቸው  አካላት መላኩን  ተናግረዋል።

ሌላው በአነስተኛ ውሃ ሳር ማብቀል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ና የተለያዩ ቅጠሎችን ተጠቅሞ ሰልፈሪክ አሲድ ያወጣ ተማሪ መኖሩን ገልፀው  ወደ ትግበራ እንዲገባ ድጋፍ ይደረግለታል ብለዋል፡፡

በቀላሉ በእጅ መጠቀም የሚቻል ማረሻ ና እግር ሲሰበር እስከ ውስጥ ገብቶ ማሰር የሚችል (ኤክስተርናል ፊክስቸር) ከተሰሩት መካከል መሆናቸውን ገልፀው በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲም ተምችን ማጥፋት የሚያስችል ምርምር ተደርጎ ውጤታማነቱ መረጋገጡን ነው የገለፁት፡፡

የምርምርና የፈጠራ ስራ ቢሰራም፣ በዩኒቨርሲቲም የተማሪዎች መመረቂያ ግኝት ወደ ተግባር የመግባት ሁኔታ ውስን መሆኑና  ቀጣይ ወደ ተግባር እንዲለወጡ ይሰራል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የፈጠራ ባለሙያዎች ድጋፍ ካገኙ በኋላ ወደ ገበያ የሚገቡቡት አሰራር ያለመኖር አፋጣኝ እገዛ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የገንዘብ ድጋፍና ሌላ እገዛ ለማድረግ የግዢ ሄደትን መጠበቅ፣ የፈጠራ ባለሙያዎቹ በሃገር አቀፍ ደረጃ ያሉ በመሆኑ  ባሉበት የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ከመስሪያ ቤቱ ተልእኮ ውጪ መሆኑም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ የሚፈልጉት እቃ በሀገር ውስጥ አለመገኘቱ ና ለግዢም በሃገር ደረጃ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ የባለሃብቶች ተባባሪ አለመሆን ሥራው ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል   ያሉት ቡድን መሪዋ፤ ኢንቨስተሮች ለምርምር ሥራ ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎችም የፈጠራ ውጤታቸውን እንዴት ወደ ቢዝነዝ እናስገባው የሚል ሰትራተጂ  በመንደፍ፣ ፈጠራውን እንዴት ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚችሉ ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውና  እንዴት   ወደ ገበያ እንደሚቀይሩትም ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የማበረታቻ ሽልማቱ  የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች  የመሞከር  አድል እዲኖራቸው አድርጓል ያሉት ወይዘሪት ሊንዳ፤ ባለሙያዎቹም በሽልማቱ በመነቃቃት በተለያየ ዘርፍ ደጋግመው እየተወደደሩ መሆኑን ገልፀው  የማብቃትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ውሱንነት እንዳለበት ተናግረዋል።

ሚኒሰቴሩ ለፈጠራ የመጀመሪያ መንደርደሪያ መሆን የሚያስችል የኢንተርኔት አገልግሎት፣ መረጃ በመሰብሰብ ዲዛይን መስራት የሚያስችል የምርምር ማእከል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን የፈጠራ ባለሙያዎቹ አስከ 6 ወራት በማእከሉ ቆይታ አድርገው እንደሚለማመዱም ተጠቅሷል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት አመትም ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች አስከ ተመራማሪነት ላሉ 186 የፈጠራ ባለሙያዎች የሳይንስና የፈጠራ  እውቅና ና ሽልማት ተሰጥቷል፡፡