ምሩቃን እወቀታቸውን በመጠቀም የሀገሪቱን የለውጥ ጉዞ ሊያግዙ ይገባል-የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር

51
ፍቼ ኢዜአ ሀምሌ 6 /2011 ምሩቃን በሰለጠኑባቸው የእውቀትና የሙያ ዘርፎች ጠንክረው በመስራት ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ሊያግዙ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ አስገነዘቡ ። የሰላሌ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዛሬ በመጀመሪያ ዲግሪ አስመርቋል። በምርቃው ስነ ስርዓት  በክብር እንግድነት የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎቹ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ሀገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ፣ የሰላምና የልማት ጉዞ ማገዝ አለባቸው ። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተስተዋሉ የፀጥታና የሰላም ችግሮች እንዳይደገሙ በሰለጠነና ከስሜታዊነት በፀዳ መንገድ በውይይት መፍታት እንደሚገባ አመላክተዋል ። በከፍተኛ ወጪ የተገነባ የሰለጠነ የሰው ኃይልና ንብረት በምንም መልኩ ጉዳት ሊደርሰበት እንደማይባ አስገንዝበዋል ። በኦሮሚያ ክልል ምክትል ኘሬዝዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማትና የለውጥ ጉዞዎች ለማሳካት የምሩቃን ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተመራቂዎች በመልካም ስነ ምግባር በመታነፅ ተመራማሪና አዳዲስ  ቴክኖሎጂ ፈጣሪ በመሆን በህብረተሰባቸው ውስጥ በጐ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳለባቸው ዶክተር ግርማ አሳስበዋል፡፡ መንግስት በሁሉም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል ። ዩኒቨርስቲው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ለጀመረው ጥረት የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደማይለየው አስታውቀዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ኘሬዝዳንት ዶክተር ገናነው ጐፌ  ተመራቂዎቹ  በልዩ ልዩ የሙያ መስኮች  ለሶስት ዓመታት  የተሰጣቸውን የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በአግባቡ ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል ። ተቋሙ በአሁን ወቅት ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ 3ሺህ 99ዐ ተማሪዎችን በአምስት ኮሌጆችና በ18 የትምህርት ዘርፎች እያሰለጠነ ነው። መንግስት ለከፍተኛ ትምህርት በሰጠው ልዩ ትኩረት በፍቼ ከተማ በሚገኘው ጀነራል ታደሰ ብሩ ካምፓስና በሌሎች ኮሌጆች ውስጥ በ73ዐ ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመሩ የህንፃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የመብራት፣ ውሃና የዲጂታል መስመር ዝርጋታ ማስፋፊያ ግንባታዎች እየተፋጠኑ መሆኑን ጠቅሰዋል ። የዩኒቨርስቲውን የሁለተኛ ዙር ግንባታ ለመጀመርም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል ። እንደ ዶክተር ገናነው ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት፣ የምርምርና የአገልግሎት አሰጣጡን ከአካባቢው ህብረተሰብ ኑሮና ምጣኔ ሀብት ጋር ለማዛመድ የሚያስችለውን አቀጣጫ  ቀይሶ ለተግባራዊነቱ እየሰራ ነው ። ከተመራቂዎች መካከል የላቀ ውጤት በማስመዝገብ የተሸለመው የዕፅዋት ሣይንስ  ተማሪ ከበደ ስዩም በትምህርት ቆይታው የቀሰመውን እውቀት በተግባር በመተርጐም የተጣለበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልጿል፡፡ “ችግሮችን ተቋቁሜ ለማዕረግ  በቅቻለሁ" ያለችው ደግሞ ተመራቂ ተማሪ ኤፍራታ ወዳጆ ናት ። በተማረችበት ሙያ ህብረተሰቡን በቅንነት በማገልገል ሀገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጻለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም