በሙያችን ሥራ ፈጥረን ህይወታችንን ለመምራት ተዘጋጅተናል--- ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሙያችን ሥራ ፈጥረን ህይወታችንን ለመምራት ተዘጋጅተናል--- ተመራቂዎች
58
ደሴ ኢዜአ ሀምሌ 6/2011 በቀሰሙት ሙያ ስራ በመፍጠር ህይወታቸውን ለመምራት መዘጋጀታቸውን በደሴ ወይዘሮ ስኀን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪዎች ገለፁ ። ኮሌጁ ከደረጃ አንድ እስከ አምስት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 500 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። በአውቶ መካኒካል ዘርፍ በደረጃ አምስት የተመረቀው ተማሪ አደም ሙሃባ በኮሌጁ ቆይታው በንድፈ ሀሳብና በተግባር ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ስራ በመፍጠር ህይወቱን ለመምራት የስነልቦና ዝግጅት ማድረጉን ተናግሯል ። በጋርመንት ዘርፍ ተመራቂ ሰማአ ይመር በበኩሏ በተመረቀችበት ዘመናዊ የወንዶችና የሴቶች ልብስ ስፌት ዲዛይን ሙያ በመሰማራት ከቤተሰብ ጠባቂነት ለመላቀቅ ራሷን ማዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡ “የግሌን ሥራ በመጀመር ለሌሎችም የስራ እድል ለመፍጠር ጭምር አቅጃለሁ” ብላለች፡፡ “ሁሉም ሰው ያለውን እውቀት ተጠቅሞ እራሱን በገቡ ለመቻል መጣር ይገባዋል” ያለችው ተመራቂዋ እውቀትና ጉልበትን በመጠቀም የራስን ሰራ ለመፍጠር መጣር እንደሚገባ መክራለች ። የኮሌጁ ዲን አቶ ጌታቸው አለምነው ኮሌጁ ምሩቃን በገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን በተግባራ የተደገፈ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ። ኮሌጁ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት በ2012 የትምህርት ዘመን በአውቶሞቲቭና ጀነራል ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ለማሰልጠን መዘጋጀቱን አመላክተዋል ። የዕለቱ የክብር እንግዳና የደሴ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ሚካኤል ከኮሌጁ የሚመረቁ ተማሪዎች በተግባር በተደገፈ እውቀት የጨበጡ በመሆናቸው በሚሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል ። የከተማው አስተዳደር ተመራቂዎች የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብተዋል ። ኮሌጅ ከተመሰረት ከ90 ዓመት በላይ እንደሆነው በምረቃው ስነሰርዓት ወቅት ተገልጿል።