ተመራቂዎች ራሳቸውን ከሥነ ምግባር ጥሰቶች በማራቅ የመልካምነት አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

75
ሀዋሳ ኢዜአ ሐምሌ 06/2011 ተመራቂዎች ራሳቸውን ከሥነ ምግባር ጥሰቶች በማራቅ ምክንያታዊነትና ሚዛናዊነትን በመላበስ የመልካምነት አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ገለፁ ፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና በድህረ ምረቃ መርሀ ግብሮች ያስተማራቸውን ዘጠኝ ሺህ 860 ተማሪዎችም ዛሬ  አስመርቋል ፡፡ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ  እንደገለጹት ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ፈታኝ ሁኔታ ለማውጣት በዕውቀትና መልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ ሚዛናዊና ምክንያዊ የሆኑ ዜጎች ያስፈልጓታል። ተመራቂዎችም ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀሉ በትምህርት ቆያታቸው ካካበቱት ዕውቀትና ክህሎት በተጨማሪ እንደ ተማረ ሰው ሚዛናዊና ምክንያታዊነትን በመላበስ ነፃ አስተሳሰብን የሚያራምድ የመልካምነት አርአያ  መሆን እንደሚጠበቅባቸው  ተናግረዋል፡፡ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው በበኩላቸው ተቋሙ ዛሬ ያስመረቃቸው  ዘጠኝ ሺህ 860 ተማሪዎች በድህረና በድህረ-ምረቃ መርሀ-ግብሮች በመጀመሪያ ፣ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያስተማራቸው መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡ ከተመራቂዎች መካከል  28 ነጥብ 4 በመቶ ሴቶች ናቸው ፡፡ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሂደቱ ባሻገር የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን በማረጋገጥ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት የቤተ ሙከራ ፣ የቤተ መጻሕፍትና ሌሎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እያከናወኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ዶክተር ኢንጂነር ፍስሃ ተመራቂዎች ኢትዮጵያ ካላት ውስን ሀብት ለትምህርት ሥራ ከፍተኛ በጀት  በመመደብ እንዳስተማረቻቸው ሁሉ አሁን ደግሞ የቀሰሙትን  ዕውቀት ፤ ክህሎትና ጉልበት ለሀገራቸው ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡ በእንስሳት ህክምና በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀው ናትናኤል አበበ በሰጠው አስተያየት በመመረቂያ ምርምር ሥራው  በሀገር ደረጃ የእንስሳት ሀብት ላይ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን መገንዘብ መቻሉን ተናግሯል ፡፡ ሀገሪቱ ባላት  ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት  ሀብት ልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነች ገልፆ በዘርፉ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ  ገልጿል። በትምህርት ፕላንና አስተዳደር በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀችው ቃልኪዳን መንክር በበኩሏ ዐይነ ስውር በትሆንም  በትምህርት ወቅት የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች የወደፊት ራዕይዋን በማሰብ በዓላማ ፅናት ማለፏን ተናግራለች ፡፡ "በቆይታችን ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖር በርካታ ልምዶችን አካብተናል "ያለችው ተመራቂዋ በሥራ ዓለምም ይህን አብሮነት የማስቀጠል ችግሮች ሲፈጠሩም መሰከነና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ገልፃለች ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም