ዓመታዊ የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የስፖርት ውድድር ተካሄደ

77
ሚዛን ሚያዝያ 24/2010 ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የልማት ድርጅቶች መካከል በሚዛን ከተማ ሲካሄድ የቆየው የስፖርት ውድድር ተጠናቀቀ፡፡ በኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ አጎራባች ዞኖች በሚገኙ የልማት ድርጅቶ መካከል ከሚያዝያ 17 እስከ ሚያዝያ 23 /2010ዓ.ም. በስድስት የስፖርት ዓይነቶች ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ድሪብሳ ለገሰ እንደገለጹት የስፖርት ውድድሩ በዓለም ለ129ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ43ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተካሄደ ነው፡፡ "የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ለሠራተኛው መብት መከበር ይሰራል ያሉት " አቶ ደሪብሳ፤በአሰሪና ሠራተኛው መካከል ጤናማ ግንኙነት ሲኖር የተቋማት ምርታማነትና ውጤታማነት እንደሚረጋገጥ ተናግረዋል፡፡ ውድድሩ ከዚህ ቀደምም በየዓመቱ ሲካሄድ እንደነበር አስታውሰው "የተቋማት ሠራተኞች እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁና አንዳቸው ከሌላኛው ልምድ እንዲለዋወጡ ያስችላቸዋል "ብለዋል፡፡ በመዝጊያው ስነስርዓት የተገኙት የቤንች ማጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ምትኩ ታምሩ በበኩላቸው "ውድድሩ በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት የሚሰሩ ሠራተኞች መብትና ግዴታቸውን እንዲገነዘቡ ከማስቻሉም በላይ የሥራ ተነሳሽነታቸውን ይጨምራል" ብለዋል፡፡ ሠራተኞች በፖለቲካዊም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ አጋዥ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ የጎጀብ እርሻ ልማት ሠራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ጥበቡ "ውድድሩ የልማት ተቋም ሠራተኞች የሥራ መነሳሳትና ጥሩ የሥራ ባህል እንዲፈጠር ያግዛል "ብለዋል፡፡ ሜይዴይ ለሠራተኛው መብት እንዲከበር መሠረት የተጣለበት ምክንያት የሆነ ታሪካዊ ዕለት በመሆኑን ሠራተኞች ትኩረት ሰጥተው እንደሚያከብሩትም አቶ ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ የልማት ድርጅቶች የተውጣጡ ሠራተኞች በስድስት የስፖርት ዓይነቶች የተሳተፉ ሲሆን ለአሸናፊዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በእግር ኳስ ውድድር ሊሙ እርሻ ልማትና ውሽውሽ ሻይ ልማት ለፍጻሜ ደርሰው ሁለት አቻ ተለያይተዋል፤ በጎል ብልጫ ሊሙ ቡና ልማት የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡ በተመሳሳይ በቦሊቦል ውድድር ጉመሮ ሻይ ልማትና ጨዋቃ ሻይ ልማት ድርጅቶች ለዋንጫ ደርሰው ጉመሮ አሸንፎ ዋንጫ ወስዷል፡፡ አዘጋጁ በበቃ ቡና ልማት የጸባይ ዋንጫ አግኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም