የሰሜን ሸዋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በችግኝ ተከላ ተጀመረ

48
ኢዜአ ሀምሌ 5/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የዘንድሮ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግኝ በመትከል በይፋ ተጀመረ ። ”በጎ ፈቃደኝነት ለለውጥ ቀጣይነት” በሚል መሪ ሀሳብ በዞኑ የሚካሄደው የዘንድሮ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ደብረብርሃን ከተማ በአበሻ አረጋዊያንና ምስኪኖች መርጃ ልማት ማዕከል በተካሄደ ችግኝ ተከላ ስነስርዓት ነው የተጀመረው። የዞኑ አስተዳደር ተወካይ  አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ በወቅቱ እንደገለፁት ወጣቶች ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተጓዳኝ በየአካባቢያቸው በሰላምና ፀጥታ ማስከበር ስራዎች በመሳተፍ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። ወጣቶች የእውቀት ደረጃና አቅማቸውን ባገናዘቡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በመሳተፍ አካባቢያቸውን ሊቀይሩ እንደሚገባም አመላክተዋል ። የዞኑ ሴቶች ህፃናትናወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ቤተ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨምሮ 460ሺህ 988 ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል ። በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ከሚከናወኑት መካከል  የማህበረሰብ ልማት ተኮር የሆኑ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የአካባቢ ጽዳትና ጥበቃ  ይገኙበታል። ኃላፊዋ እንዳሉት የአካባቢ ሚዛንን ለመጠበቅ አስተዋጽኦ ያላቸው 21 ሚሊዮን የዛፍ ችግኞች ተዘጋጅተዋል፤  2ሺህ 500 ዩኒት ደም ለማሰባሰብ  ታቅዷል። ለሁለት ወራት በሚቆየው የበጎ ድቃድ አገልግሎት ከ42  ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ ይጠበቃል ። በደብረብርሃን ከተማ የቀበሌ  ሶስት ነዋሪ ወጣት ወርቁ ተክለሚካኤል የማህበረሰቡን ችግሮች ለማቃለል  በሚረዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እንደሚሳተፍ በሰጠው አስተያየት ገልጿል ። "የእረፍት ጊዜዬን እውቀቴን በመጠቀም ማህበረሰቡን ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ " ያለችው ደግሞ በከተማው የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ወጣት ፍቅርተ ወሰኔ ናት። በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ  ስነ ስርዓት ወቅት ከዞኑ 21 ወረዳዎችና ከስድስት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ100 በላይ በጎ ድቃደኞች ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም