የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከኡጋንዳ አቻቸው ዮዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተወያዩ

106

ሐምሌ 5/2011 የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ እና የኡጋንዳ አቻቸው ዮዌሪ ሙሴቬኒ በሃገራቱ መካከል ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ለማርገብ የሚያስችል ውይይት በአንጎላ ማካሄዳቸውን ይፋ ሆኗል።

ሲ ጂ ቲ ኤን እንደዘገበው የሁለቱ መሪዎች ውይይት በታላላቅ ሃይቆች አካባቢ በሚኖረው ሰላም ዋስትና ሊሰጥ ይችላል ነው የተባለው።

መሪዎቹ የተገናኙት በአንጎላው ፕሬዚዳንት ጋባዥነት በአንጎላ ዋና ከተማ ላውንዳ የአንድ ቀን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ዕድሉ ከተመቻቸ በኋላ እንደሆነ የአካባቢው የዜና ምንጮች ጠቁመዋል።

ካምፓላ እና ኪጋሊ እኤአ ከ2017 ጀምሮ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ግንኙነታቸው በመሻከሩ በድንበሮቻቸው አካባቢ በሚያካሄዱት የሸቀጦች ልውውጥ ላይ ተፅዕኖው አሳድሮ እንደቆየም ዘገባው አስታውሷል።

ሩዋንዳ የኡጋንዳ መንግስት አማፂያንን እንዲሁም የሩዋንዳ መንግስት ተቃዋሚዎችን ትረዳለች በሚል በአንፃሩም ኡጋንዳ ኪጋሊ በድብቅ ስለላ ታካሂድብኛለች በሚል እርስ በርስ ሲካሰሱ መቆየታቸውም  ተዘግቧል።

እንደ ዘገባው የአንጎላው ስብሰባ የዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ አማፅያንን ጉዳይ አንስቶ ሊወያይ እንደሚችል ተጠብቋል።

የኮንጎው ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ተሽከዲ ሁለቱ ሃገራት የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተስፋቸውን ገልፀዋል ሲልም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ሩዋንዳ፣ አንጎላና ኡጋንዳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኮንጎ ስደተኞችን አስጠልለው እንደሚገኙም ዘገባው አመልክቷል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅትም የሃገራቱ መሪዎች በምስራቃዊ ኮንጎ ከ1,600 በላይ  ሰዎች በኢቦላ በሽታ በሚሰቃዩበት ጉዳይ ዙሪያም ውይይት ያካሂዳሉ ተብሎ እንደሚጠብቅም ዘገባው ያሳያል፡፡