የጋራ መኖሪያ ቤቶቸን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ የወጣው መመሪያ ሕገ መንግስቱን የሚጣረስ አንቀጽ አለው

87
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 5/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎችና ለልማት ተነሺዎች ለማስተላለፍ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2008 አንቀጽ 44 (ሐ) እና (ሠ)  የህገ መንግስቱን አንቀጽ 40 ድንጋጌዎ ሌሎች መርሆዎችንች የሚቃረን መሆኑን የህገ መንግሰት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጉባኤው ጉዳዩን የተመለከተው በአንድ አመልካችና በአስተዳደሩ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ መሀከል ሲካሄድ የነበረውን ክርክር ተከትሎ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት መመሪያ እንዲመረመር በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት  ስለተላከለት ነው። በመመሪያው አንቀጽ 44 የቤት እድለኛ በሞተ ጊዜ እድሜያቸው 18 የሞላቸው የሟች ልጆች በሟች ስም የወጣውን ቤት አይወርሱም በማለት ደንግጓል። ይህ ደግሞ በሟች ወራሾች መካከል ልዩነት በመፍጠር ቤት የሌላቸው ግለሰቦች በውርስ መልክ የሚያገኙትን የቤት ባለቤትነት መብት የሚሸራርፍ ነው በማለት አጣሪ  ጉባኤው አስታውቋል። በዚህም ጉባኤው የተጠቀሰው አንቀጽ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 40 መሰረት የተደነገገውን የዜጎች የንብረት የማፍራት  መብት የሚያጣብብ እና ከሌሎች የህገ መንግስቱ መርሆዎች ጋር የሚጋጭ ሆኖ እንዳገኘውም ገልጿል። ስለሆነም የመመሪያው አንቀጽ 44 (ሐ) እና (ሠ) የህገ መንግስት ትርጓሜ ያስፈልገዋል በማለት ለመጨረሻ ውሳኔ ጉዳዩን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩን አስታውቋል። የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 82 መሰረት  ተቋቁሞ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት ለማስከበር የሚሰራ ተቋም ነው
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም