በጎንደር ሁከት በመፍጠርና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ 73 ግለሰቦች ምርመራ እየተደረገባቸው ነው

105
ጎንደር ኢዜአ ሐምሌ 5 ቀን 2011 በጎንደር ከተማ ሰሞኑን በተፈጠረው ሁከት ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ 73 ግለሰቦች ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ኮማንደር ማረልኝ ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በተጠረጠሩበት ወንጀል አስፈላጊው ማጣራት እየተደረገባቸው ነው። ምርመራው እንደተጠናቀቀ ጥፋተኞ የሆኑት ግለሰቦች ጉዳይ አግባብ ወዳለው የፍትህ አካል እንደሚቀርብ አስረድተዋል። ‹‹ፖሊስ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ  ተጠናክሮ ይሰራል›› ብለዋል። ኅብረተሰቡም የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ያደረገውን አስተዋፅኦም አድንቀዋል፡፡ በሁከቱ ከ30 በላይ የንግድ ሱቆችና ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጹት ኮማንደር ማረልኝ፣የጉዳቱን ጠቅላላ ግምት  ለማወቅ በምርመራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ አካላትና ኅብረተሰቡ ተቀናጅተው በመስራታቸው ሁከቱ ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡ ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ንብረት ቢሆነኝ ሰላምን በሚያደፈርሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ህግ በማስከበር ሂደቱ ንፁሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እንዲደረግ አመልክተዋል፡፡ ሌላኛው ነዋሪ አቶ ገበየ ደስታ በበኩላቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ጥፋት የሚያደርሱ አከላት ቅጣት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡ በጎንደር ከተማ ሁከት ለመፍጠር የተሞከረው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ  ላይ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም